ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር እያሴሩ ያሉ ምዕራባውያን ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል-ሩሲያ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ ለኢትዮጵያ ታማኝ እና አስተማማኝ አጋር ሆና እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴርኪን ተናገሩ፡፡
አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴርኪን ከሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ሩሲያ እና ኢትዮጵያ 120 ዓመታትን የተሻገረ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን አውስተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት በብዙ መስኮች እየተጠናከረ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡
“ከ 19ኛው መቶ ክፍለ-ዘመን ጨምሮ የሀገራቱ ግንኙነት በጥሩ ሁኔታ እያደገ መጥቷል ያሉት አምባሳደሩ÷ ሩሲያ ለኢትዮጵያ አስተማማኝ እና ታማኝ አጋር ነች ብለዋል፡፡
የሩሲያ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ዘመን በሚሻገር ወዳጅነት፣ ትብብር እና መከባበር ላይ የተመሰረተ መሆኑንም አነውስተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሩሲያ እና ኢትዮጵያ ትስስራቸውን በዲፕሎማሲ እንዲሁም በንግድና በምጣኔ ሃብታዊ መስኮች አጠናክራረው ለመቀጠል እየሰሩ መሆናቸውን አምባሳደሩ ጠቁመዋል፡፡
በሰኔ ወር በኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና በሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ መካከል የተካሄደውን ምክክር ያስታወሱት አምባሳደሩ÷ይህም በሁለቱ ሃገራት መካከል እየተካሄው ያለው ያላሰለሰ ፖለቲካዊ ውይይት እያደገ የመጣውን የሁለቱን ሃገራት ጠንካራ ወዳጅነት የሚያመላከት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በወታደራዊ ቴክኒካል ትብብር እና ሰላማዊ የኒውክሌር ሃይል ልማት ዘርፎች ሃገራቱ የፈፀሟቸውን ስምምነቶች ወደ ተግባራዊ ውጤት ለመለወጥ በሁለቱም በኩል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያን ጊዜው በደረሰበት ቴክኖሎጂ ማስታጠቅ እና ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማቷን ማፋጠን የስምምነቱ ዋነኛ አላማ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡
ባለፈው በተካሄደው የተመባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ሀገራቸው ሩሲያ የአውሮፓ ሃገራትንና የአሜሪካን አቋም በሚቃረን መልኩ ከኢትዮጵያ ጎን መቆሟን ያወሱት አምባሳደሩ÷ ሁለቱ አገራት በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ ፍትህን እና ዴሞክራሲን የሚደግፍ ተመሳሳይ አቋም ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሩሲያ በትግራይ ያለው አሁናዊ ሁኔታ በኢትዮጵያውያን በራሳቸው የሚፈታ የኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ነው ብላ እንደምታምን ተናግረዋል፡፡
የመንግስታቱን ድርጅት የጋራ ሰነድ ሽፋን አድርገው ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር እያሴሩ ያሉ ምዕራባውያን ሃይሎች ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል ሲሉም አክለዋል፡፡
ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ጉዳዩን በጫና እና በማስፈራራት ለመፍታት እየተሞከረ ያለውን አካሄድ ሩሲያ እንደምታወግዘውና ከዚህ ጋር ተያይዞ ሀገራቸው ለኢትዮጵያ ያላት ድጋፍ የማይናወጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
2013 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን የህዳሴ ግድብን ሁለተኛ ሙሌትን፣ 6ኛውን ምርጫ እና ሌሎችንም ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግባራትን በስኬት ያጠናቀቁበት ዓመት መሆኑን አንስተው÷ መጪው ዘመንም ለመላው ኢትዮጵያውያን የሰላም፣ የብልፅግና እና የፍስሃ እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡
በወንደሰን አረጋኸኝ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!