Fana: At a Speed of Life!

ኢራን አሜሪካ ከኒውክሌር ስምምነቱ በመውጣቷ ሳቢያ ለደረሰባት ኪሳራ ካሳ የምታገኝ ከሆነ መነጋገር እንደምትችል አስታወቀች

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ቴህራን አሜሪካ ከኒውክሌር ስምምነቱ በመውጣቷ ሳቢያ ለደረሰባት ኪሳራ ካሳ የምትከፍልና ይቅርታ የምትጠይቅ ከሆነ ከዋሽንግተን ጋር መነጋገር እንደምትችል አስታወቀች።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዋሽንግተን ከኢራን ጋር በኒውክሌር መርሃ ግብሯ ዙሪያ መወያየት ትፈልጋለች በሚል ተደጋጋሚ የእንወያይ ጥያቄዎችን ማቅረባቸው ይታወሳል።

ፕሬዚዳንቱ ሃገራቸው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመደራደርና ከፕሬዚዳንት ሮሃኒ ጋር በአካል ተገናኝተው የመወያያት ፍላጎታቸውንም በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።

ኢራን በበኩሏ የአሜሪካን ግብዣ ለማስመሰል የሚደረግ ነው ስትል በተደጋጋሚ ስታጣጥለው ቆይታለች።

የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ሃሰን ሮሃኒም “አሜሪካ ከ2015ቱ የኒውክሌር ስምምነት በመውጣቷ ምክንያት ቴህራን ለደረሰባት ጉዳት ዋሽንግተን ይቅርታ ጠይቃ ማካካሻ የምትሰጥ ከሆነ አሁንም ቢሆን ከዋሽንግተን ጋር መነጋገር እንችላለን” ብለዋል።

አሜሪካ ግዴታዋን ከፈጸመች ለመነጋገር ችግር የለብንም ያሉት ሮሃኒ አሁን ላይ ንግግር እንዲደረግ የሚቀርቡ ግብዣዎችን ከቃላት የማይዘሉና ሃሰተኛ ናቸው ሲሉም ተደምጠዋል።

እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጅ በጉዳዩ ላይ ከአሜሪካ በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም።

የሃገራቱ ግንኙነት በተለይም የኢራን ብሄራዊ አብዮት ዘብ ጠባቂ ሃይል አዛዥ ጄኔራል ቃሲም ሱለይማኒ በአሜሪካ ድሮን በተፈጸመ ጥቃት ከተገደሉ ወዲህ እጅጉን ሻክሯል።

ከዚያን ጊዜ ወዲህም ቴህራን ከዋሽንግተን የቀረበላትን የእንነጋገር ጥያቄ ውድቅ በማድረግ በጫና አልደራደርም ስትል ቆይታለች።

አሜሪካም ኢራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን እንደምትጥል ትገልጻለች።

እስከዚህ ሳምንት መጨረሻ ድረስም በቴህራን ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችላትን የውሳኔ ሃሳብ ለፀጥታው ምክር ቤት አስገብታለች።

የአሜሪካ የውሳኔ ሃሳብ ተቀባይነት ካገኘ ሃገራት ከፀጥታው ምክር ቤት እውቅና ውጭ ለኢራን ምንም አይነት መሳሪያ መሸጥም ሆነ ማስተላለፍ አይችሉም።

ይህ እንዲሆን ግን የውሳኔ ሃሳቡ ከምክር ቤቱ 9 ድምጾችን ማግኘትና ከሩሲያ፣ ብሪታን፣ ቻይና እና ፈረንሳይ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ተቃውሞ ሊያስተናግድ አይገባም፣

ምንጭ፡- አር ቲ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.