ብልፅግና የሀገር ህልውናን ለመታደግ ድርብ ሃላፊነት የወሰደ ፓርቲ ነው- ጠ/ሚ ዐቢይ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ብልፅግና የሀገር ህልውናን ለመታደግ ድርብ ሃላፊነት የወሰደ ፓርቲ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለፁ።
የብልፅግና ፓርቲ የፌደራል እና ክልል አቀፍ የአመራሮች ሥልጠና ከየካቲት 17 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል።
የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዐቢይ አህመድ በመላ ሀገሪቱ በስልጠና ላይ ለቆዩ የፓርቲው አመራሮች በዛሬው እለት ማጠቃለያ መልእክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም ብልፅግና የሀገርን ህልውናን ለመታደግ ድርብ ሀላፊነትን የወሰደ ፓርቲ መሆኑን አንስተዋል።
ኢህአዴግ በሞት አፋፍ ላይ የነበረ ድርጅት እንደነበረ ያስታወሱት የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዐቢይ፥ አዲስ ሀይል፣አዲስ ጉልበት በመያዝ ራሱን እንደ አዲስ የፈጠረ ፓርቲ ነውም ብለዋል።
አሁን በሀገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ጥልቅ እና ፈጣን መሆኑንም አንስተዋል።
በአንድ ሀገር ውስጥ ዴሞክራሲ ዕውን የሚሆነው የህግ የበላይነት ሲከበር ነው ያሉት ዶክተር ዐቢይ፥ “የህግ የበላይነትን የማስከበር ሁኔታ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፤ ህግ ማስከበር የመጀመሪያ ስራችን ዋና ተግባራችን ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
የትግራይ ህዝብ የብልፅግና ዋና ደጋፊ ነው፣ ምንም እንኳ ብልፅግና ስሙ እንዲጠፋ የሚሰሩ ለውጥ የማይፈልጉ ሀይሎች ቢኖሩም፥ የትግራይን ህዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የግድ ነው ሲሉም አንስተዋል።
ከህገ መንግስቱ ጋር ተያይዘው በሚነሱ ጉዳዮች ላይም ህገ መንግስቱን በረጋና በሰከነ መንገድ፣ በውይይትና በህገ መንግስታዊ አካሄድ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ብልፅግና የሀሳብ ድህነት የሌለበት ፓርቲ ነው ያሉት ዶክተር ዐቢይ፥ “ብዙ የተፃፉና የተሰነዱ ሀሳቦች አሉት፤ እነዚህን ሀሳቦች ወደ ተጨባጭ ተግባር ማስገባት ያስፈልጋል” ሲሉም ተናግረዋል።
ከሀገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞም፥ “ምርጫው በተያዘለት ጊዜ የሚካሄድ ነው የሚሆነው፤ ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ እንዲሆን የሁሉም ሀላፊነት ነው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ እውነተኛ ፌደራሊዝም የሚተገበርባት ሀገር እንድትሆን ብልፅግና አበክሮ እንደሚሰራም አስታውቅዋል።
“ለብልፅግና እውቀት ሲደመር እውነት እኩል ይሆናል ውጤት ነው፤ የሚመጣው ውጤት ደግሞ በጥራቱ የሚፈተሽ መሆን አለበት” ብለዋል።
“መደመር መነሻውንም መዳረሻውንም ሰው ላይ ያደረገ ዕሳቤ ነው” ያሉት የፓርቲው ፕሬዚዳንት፥ “መደመር መንገዳችን ብልፅግና ደግሞ መዳረሻችን ነው” ብለዋል።
“መደመር መስመር መንገድ ነው፤ በዚህ ጉዟችን ደግሞ የኢትዮጵያን ብልፅግና እናረጋግጣለን” ሲሉም ተናግረዋል።
ክልል ከመሆን ጥያቄ ጋር ተያይዞም ብልፅግና ፓርቲ የክልልነት ጥያቄ እንዳይነሳ አይልም ያሉት ዶክተር ዐቢይ፥ ዋናው ቁም ነገሩ ከህዝቡ ተጠቃሚነት አኳያ ነው መመዘን ያለበት፤ ለዚህ ደግሞ ውይይት ክርክር ጥናት ያስፈልጋል ብለዋል።
ክልል በመፍጠር ሂደት ውስጥ ሀገር እንዳይፈርስ ቆም ብሎ ማሰብ እና ማጤን ለጋራ ተጠቃሚነት መስራት እንደሚያስፈልግም በማከል።
ከህዳሴ ግድብ ሰሞንኛ ጉዳይ ጋር ተያይዞም “ከውጭ ለምናገኘው ሀብት ብለን ሀገራዊ ክብራችንን አሳልፈን አንሰጥም” ብለዋል።
ግድቡን የሌሎችንም ሀገራት ጥቅም በማይጋፋ መልኩ አጠናቀን ጥቅም ላይ እናውለዋልን ሲሉም ተናግረዋል።
“ምንም እንኳ ቀደም ብለን ማጠናቀቅ ቢኖርብንም፤ በባለፈው ሳንቆጭ የያዝነውን ሳንለቅ ግድቡን አጠናቀን የህዝባችንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስራት ያስፈልጋልም” ብለዋል።