በደራሼ ልዩ ወረዳ በተከሰተው ግጭት እጃቸው እንዳለባቸው የተጠረጠሩ ከ300 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ በቅርቡ በተከሰተው ግጭት እጃቸው እንዳለባቸው የተጠረጠሩ ከ300 በላይ ግለሰቦች በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለማየሁ ማሞ ዛሬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት÷ ከሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓም ጀምሮ በደራሼ ልዩ ወረዳ በታጠቁ ፀረ ሰላም ኃይሎች የጸጥታ ችግር በመከሰቱ ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ተከስቷል፡፡
ይህን ተከትሎ የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስና የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል ኮማንድ ፖስት አካባቢውን ለማረጋጋትና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከህብረተሰቡ ጋር ሲሠራ ቆይቷል፡፡
የወረዳው ሕዝብ ከፀጥታ ጥምር ኃይል ጋር ባደረገው ትብብር ለአካባቢው ቀውስ እጃቸው እንዳለበት ተጠረጠሩ 316 ሰዎች በሕግ ቁጥጥር ሲሆኑ በርካታ የጦር መሣሪያዎችም መያዙን ገልጸዋል፡፡
እንደኮሚሽነሩ ገለጻ በአሁኑ ሰዓት የመንግስት መስሪያ ቤቶች በከፊል ስራ የጀመሩ ሲሆኑ የሕዝቡ ማህበራዊ እንቅስቃሴም ወደ ቀድሞው እየተመለሰ ይገኛል ብለዋል፡፡
የአካባቢውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግና ቀሪ ግለሰቦችን ከነጦር መሣሪያቸው ለመያዝ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ከሕዝቡ ጋር በተዋረድ እየተመከረ መሆኑን ጠቅሰው÷ በዚህም ጥሩ ውጤት እየታዬ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ኮማንድ ፖስቱ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር አብሮ እንደሚሠራም ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡