በደምቢ ዶሎ ከታገቱ ተማሪዎች መካከል 21 መለቀቃቸው ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከታገቱ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ውስጥ 21 መለቀቃቸውን እና ቀሪ 6 ተማሪዎችን ለማስለቀቅ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።
የጠቅላይ ሚንስትሩ የፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ እገታ ተፈጽሟል መባሉን ተከትሎ በሁኔታው ዙሪያ ለኢቢሲ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አቶ ንጉሱ በማብራሪያቸው፥ ሰሞኑን በደምቢ ዶሎ ብቻ ሳይሆን በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ 16 በሚጠጉ ዩኒቨርሲቲዎች የፀጥታ ችግሮች እንደነበረ በማንሳት፤ በዚህም ወደ 35 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ወደየቤታቸውና ወደ ሌሎች አካባቢዎች ዩኒቨርሲቲዎቹን ለቀው ሄደዋል ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲዎቹ ያጋጠሙትን ችግሮች ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ የቦርድ አመራሮች እና ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመወያየት አቅጣጫ ማስቀመጣቸውንም አስታውሰዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲዎችን ሁኔታ የሚያይና የማረጋጋት ስራ የሚሰራ ቡድን መዋቀሩን እንዲሁም በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የፌደራል ፖሊስ የፀጥታ ማስከበር ስራ እንዲሰራ ትእዛዝ ተላልፎ የማረጋጋት ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህም ባሻገር የአመራር ችግር ባለባቸው ዩኒቨርሲቲዎች የማስተካከያ ስራ መሰራቱን እና ከችግሮች ጋር ተያይዞ ጥፋተኛ የሆኑ ተማሪዎች እና የዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች ላይ እርምጃ መወሰዱንም አንስተዋል።
ችግር ከተከሰተባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንዱ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ነው ያሉት አቶ ንጉሱ፥ በዩኒቨርሲቲው ግጭት ሲከሰት በስጋት ከጊቢ ወጥተው ጉዞ ላይ ያሉ ተማሪዎች ጫካ ውስጥ መታገታቸውን ገልፀዋል።
የታገቱ ተማሪዎችን ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ በማንም ላይ ጉዳት ሳይደርስ ማስለቀቅ ተገቢ በመሆኑ እና የመንግስትም ቀዳሚ ስራ በመሆኑ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከአካባቢው ወጣቶች፣ ከመከላከያ ሰራዊት እና ከሌሎች የፀጥታ መዋቅር ጋር ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
በዚህም ታግተው ከነበሩ ተማሪዎች መካከል 13 ሴቶች እና 8 ወንዶች፤ በድምሩ 21 ተማሪዎች በሰላም መለቀቃቸውን ገልፀዋል።
እስካሁንም አንድ የአካባቢውን ወጣት ተማሪ ጨምሮ 6 ተማሪዎች ታግተው እንዳሉ በስፍራው ስራውን ከሚያስተባብረው የፀጥታ መዋቅር መረጃ አግኝተናል ያሉት አቶ ንጉሱ፥ ጉዳዩን በሰላማዊ ሁኔታ ለማጠናቀቅ እና ልጆቹ ላይ ጉዳት ሳይደርስ እንዲወጡ ለማድረግ የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች በአካባቢው ወግና ባህል መሰረት እንዲሁም የፀጥታ አካላት ተገቢውን ስራ እየሰሩ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የተለያዩ አካላት በቁጥርም ደረጃ የተለያዩ መረጃዎችን እየሰጡ ነው ያሉት አቶ ንጉሱ፥ በአካባቢው መንግስት ያሰማራው የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ እና የአካባቢው የፀጥታ መዋቅር በጋራ የገመገመው እስካሁን አንድ የአካባቢውን ወጣት ተማሪ ጨምሮ 6 ተማሪዎች እንደታገቱ ናቸው ብለዋል።
ቀሪዎቹን ተማሪዎች በሰላማዊ መንገድ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ለማስለቀቅ፤ መንግስትም የአካባቢው ብህረተሰብም እየሰሩ መሆኑን ነው አቶ ንጉሱ የተናገሩት።
ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ አስፈላጊውን መረጃ በየጊዜው ለህብረተሰቡ እናደርሳለን ብለዋል።