በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ የተጠረጠሩት ጥላሁን ያሚ እና አብዲ አለማየሁ ፍርድ ቤት ቀርበዋል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ገድለዋል ተብለው የተጠረጠሩት ጥላሁን ያሚ እና አብዲ አለማየሁ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል ፡፡
በከሰአት በኋላ በነበረው ችሎትም የአርቲስት ሃጫሉ ግድያን ተከትሎ በቡራዩና አዲስ አበባ በተፈጠረ አመጽና ሁከት በደረሰ የሰውና የንብረት ጉዳት የተጠረጠሩ 8 ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
በጠዋቱ ችሎት በቀዳሚነት የቀረቡት ጥላሁን ያሚ እና አብዲ አለማየሁ ላይ መርማሪ ፖሊስ የሰራውን የምርመራ ስራ ይፋ አድርጓል።
በዚህም የምስክር ቃል መቀበሉን፣ ወንጀሉ የተፈጸመበት ስፍራን በቴክኒክ ማስረጃ ማረጋገጡን፣ ግብረ አበሮቻቸውን በቁጠጥር ስ ርአውሎ ምርመራ እየሰራ መሆኑን፣ አርቲስት ሃጫሉ የተገደለበትን ሽጉጥ ከተጠርጣሪዎች ቤት ከተቀበረበት ጓሮ ማውጣቱን እና በምርመራ ማረጋገጡን አስረድቷል፡፡
ከዚህ ባለፈም በተጠርጣሪዎች እጅ ላይ የተገኘ ስልካቸውን ወደ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት መላኩን የአስከሬን ምርመራ ውጤት እየተጠባበቀ መሆኑን ገልጾ ድርጊቱ የታቀደ መሆኑን በምርመራ ማረጋገጡን ተናግሯል።
ከተጠርጣሪዎቹ በስተጀርባ ያለውን በጥንቃቄ እየመረመረ መሆኑን በመጥቀስም ከኢትዮ ቴሌኮም ያገኘውን በስልካቸው የተላከ ሰፊ መልዕክት እየተነተነ መሆኑን አስረድቷል።
ለተጨማሪ ምርመራም 14 ቀን ጠይቋል።
ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው የእስር አያያዛቸው ብርሃን የማያገኙበት መሆኑን አቤቱታ አስመዝግበዋል።
ፍርድ ቤቱም አያያዛቸው እንዲስተካከል ለፖሊስ ትዛዝ በመስጠት ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀን በመፍቀድ ውጤቱን ለመጠባበቅ ለነሃሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰቷል።
በሌላ በኩል ከሰአት በነበረ የችሎት ውሎ የአርቲስት ሃጫሉ ግድያን ተከትሎ በቡራዩና አዲስ አበባ በተፈጠረ አመጽና ሁከት በደረሰ የሰውና የንብረት ጉዳት የተጠረጠሩ በጃምባ ሁሴን መዝገብ የተካተቱ 8 ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
መርማሪ ፖሊስ ባሳለፍነው ሃምሌ 7 ቀን 2012 ዓ.ም በተሰጠው ተጨማሪ ጊዜ የሰራውን ምርመራ አቅርቧል።
በዚህም በ5ኛና 6ኛ ተጠርጣሪዎች ላይ የወንጀል ተሳትፎ መለየቱን 10 የተከሳሽ 20 ደግሞ የምስክር ቃል መቀበሉን ገልጿል።
በአዲስ አባባ ገቢዎች ቢሮ፣ መንገዶች ባለስልጣን፣ ቦሌ ክፍለ ከተማ የደረሰውን አጠቃላይ ከ136 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት መድረሱን ማስረጃ ሰብስቤያለሁም ብሏል።
በቡራዩ በተነሳ ሁከት 4 ሰዎች መሞታቸውን እና አራት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል ጠቁሟል።
ከተለያዩ ተቋማት ማስረጃ ለመሰብሰብ ተጨማሪ ምርመራ ለማከናወን 14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ የጠየቀ ሲሆን የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃም የተጠቀሰው ምክንያት ተጨማሪ ጊዜ የሚያሰጥ አይደለም ለማሰር ብቻ ነው ሲሉ ተቃውመዋል።
ተጠርጣሪዎች ከቤተሰብ ጋር እንደማይገኛኙ በድጋሚ አቤቱታ አስመዝግበዋል።
ፖሊስም ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን የአቶ በቀለ ገርባ ሁለት ልጆችን ጨምሮ አምስት ተጠርጣሪዎችን ለቀናል እኛ ለማሰር ብቻ አይደለም እየሰራን ያለነው ለምርመራ ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱም በድጋሚ አያያዛቸው እንዲስተካከል እና ከቤተሰብ ጋር በጥንቃቄ እንዲገናኙ ትዕዛዝ በመስጠት ለፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ ሰባት ቀን ጊዜ ፈቅዷል።
የምርመራ ውጤቱን ለመጠባበቅም ለሃምሌ 24 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ።
በታሪክ አዱኛ