Fana: At a Speed of Life!

ሱዳን ኢትዮጵያ 1 ሺህ ሜጋ ዋት ሃይል እንድትሸጥላት ጠየቀች

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 29 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሱዳን አንድ ሺህ ሜጋ ዋት ሃይል ለመግዛት መጠየቋን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ገለጸ።
 
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የኮርፖሬት ፕላኒንግ ስራ አስፈፃሚ አቶ አንዱዓለም ሲዓ እንደገለጹት÷ ሱዳንን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል ለመግዛት ፍላጎት አሳይተዋል።
 
ቀደም ሲል ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ እና ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ሃይል የመግዛት ፍላጎት አሳይተው ድርድር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
 
በቅርቡ ሱዳን አንድ ሺህ ሜጋዋት ሃይል እንደምትፈልግ ማሳወቋን ጠቁመው፤ ተቋማቸው ከሱዳን ባለሙያዎች ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አቶ አንዱዓለም ተናግረዋል።
 
ባለፈው ወር የተቋሙ ሠራተኞች ወደ ካርቱም አቅንተው እንደነበረና የሱዳን ባለሙያዎችም በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ውይይቱ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
 
ለኬንያ የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት 500 ኪሎ ዋት መሸከም የሚችል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ እየተጠናቀቀ መሆኑን የገለጹት አቶ አንዱዓለም÷ የኬንያ ፓርላማ ተወካዮች በቀጣዩ ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በጉዳዩ ላይ ውይይት እንደሚያደርጉም አብራርተዋል።
 
ኢትዮጵያ ከኬንያ አልፎ ታንዛኒያ እስከ ደቡብ አፍሪካ ሁለት ሺ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ የሚያስችል መሠረተ ልማት መዘርጋቷንም ተናግረዋል።
 
ሶማሌላንድም ከኢትዮጵያ ሃይል ለማግኘት እንድትችል በዓለም ባንክ ድጋፍ ኢስት አፍሪካ ፖወር ፖሊሲ ከሚባል ተቋም ጋር ጥናት እየተደረገ መሆኑ አመልክትዋል።
 
ደቡብ ሱዳንም ሃይል እንዲቀርብላት በደብዳቤ ፍላጎቷን መግለጿን ጠቁመው፤ ይህን ተከትሎ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ማከናወን የሚያስችል ጥናት ለማድረግ የባለሙያዎች ቡድን በቅርቡ ወደ ደቡብ ሱዳን እንደሚያቀና ተናግረዋል።
 
አቶ አንዷለም  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ትልቅ ፋይዳ አለው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
አገሮቹ አሁን እያሳዩት ያለው የኤሌክትሪክ ሃይል ፍላጎትም በግድቡ ያላቸውን ተስፋ እንደሚያመላክት አብራርተዋል።
 
“ኢትዮጵያም ጠንክራ በመስራት ከእራሷ አልፋ ለአፍሪካ ኩራት ትሆናለች” ብለዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.