ምርት ገበያው በሰኔ ወር 62 ሺህ 542 ቶን ምርት አገበያይቷል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሰኔ ወር 62 ሺህ 542 ቶን ምርት በ3 ነጥብ 72 ቢሊየን ብር ማገበያየቱን አስታወቀ።
በሃያ ሁለት የግብይት ቀናት ውስጥ አምስት የተለያዩ ምርቶችን ግብይት ከመፈጸሙ ባለፈ ለግብይት የሚመጣው የምርት መጠንም ጨምሯል ነው ያለው።
በግብይቱ ቡና 44 በመቶ በመጠን 66 በመቶ በዋጋ በመሸፈን ቀዳሚ ሲሆን ካለፈው ወር ጋር ሲነጻጸርም በመጠን የ6 ቶን በዋጋ ደግሞ 7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
በሰኔ ወር ለውጭ ገበያ የቀረበ 18 ሺህ ቶን ያልታጠበ ቡና በ1 ነጥብ 46 ቢሊየን ብር እና 419 ቶን የታጠበ ቡና በ53 ሚሊየን ብር ተገበያይቷል።
21 ሺህ 943 ቶን ሰሊጥ በ944 ሚሊየን ብር የተገበያየ ሲሆን ካለፈው ወር ጋር ሲነጻጸር በመጠን 40 በመቶ በዋጋ ደግሞ 39 ከፍ ብሏል።
የሰሊጥ አቅርቦት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በሶስት እጥፍ መጨመሩን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አስታውቋል።