የሀገር ውስጥ ዜናዎች (8273)

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 8 ፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) በአመት 278 ሺህ ቶን ስኳር የማምረት አቅም ያለው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 የስኳር ፕሮጀክት ግንባታ ተጠናቆ በያዝነው አመት ማብቂያ ወደ ምርት ይገባል ተባለ።

የኦሞ ኩራዝ የስኳር ልማት ፕሮጀክት በደቡብ ክልል የኦሞ ወንዝን በሚጋሩት ደቡብ ኦሞ ፣ ቤንች ማጂና ካፋ ዞኖች የሚገኙ ወረዳዎችን ያካልላል።

በፕሮጀክቱ አምስት የስኳር ፋብሪካዎችን ለመገንባት 250 ሺህ ሄክታር መሬትም ተዘጋጅቷል።

ለስኳር ፋብሪካዎቹ ግንባታ ታስቦ በመከናወን ላይ የሚገኙ የመስኖ ፣ መንገድ እና ሌሎች የመሰረተ ልማትና የማህበራዊ ተቋማት ግንባታም ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ከሚገነቡት አምስት ፋብሪካዎች ውስጥ ከሶስቱ ከእያንዳንዳቸው 12 ሺህ ቶን ፣ ከሁለቱ ደግሞ 24 ሺህ ቶን የስኳር ምርት እንደሚገኝም ተጠቁሟል።

ከነዚህም ውስጥ በደቡብ ኦሞ ዞን በግንባታ ላይ ያለው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 የስኳር ፕሮጀክት ከ80 በመቶ በላይ መጠናቀቁ ተገልጿል።

በፕሮጀክቱ ለእርሻ ልማት የሚውል 25 ሺህ ሄክታር መሬትም የተከለለ ሲሆን ግንባታ በያዝነው አመት ማብቂያ ተጠናቆ ወደ ምርት ይገባል ነው የተባለው።

በፕሮጀክቱ ዙሪያ የሚኖሩ 16 አርብቶ አደር ብሄረሰቦች ወደ ከፊል አርሶ አደርነት እየቀየሩ ሲሆን ፥ የማህበረሰቡን ህይወትም ከወዲሁ መለወጥ መጀመሩን በስፍራው ጉብኝት ያደረገችው  ባልደረባችን መሰረት ገዛኸኝ ዘግባለች።

 

 

 


አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 8 ፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) በአዲስ አበባ እየተገነቡ ያሉ የ40 /60 ቁጠባ ቤቶች እስከ ሰኔ 30 ድረስ ይጠናቀቃሉ ተባለ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ዛሬ በሰጠው መግለጫ የቤቶቹ ግንባታ እስከ 58 በመቶ ደርሷል ብሏል።

የኢንተርፕራይዙ ስራ አስኪያጅ አቶ ክንዴ ብዙነህ ፤ በሰንጋ ተራና በክራውን በ2005 ዓ.ም የተጀመሩ የ40 / 60 የቤቶች ግንባታ ከ58 በመቶ በላይ መጠናቀቃቸውን ገልጸው ፥ በ2006 ዓ.ም የተጀመሩ የቤቶች ግንባታም እስከ 20 በመቶ ተጠናቀዋል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ 13 ሺህ 881 ቤቶች በግንባታ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

በዚህም በሰንጋ ተራ 410 ቤቶች ፣ በክራውን ሳይት 880 ቤቶች በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ ሲሆን ፥ አፈፃፀማቸውም  58 በመቶ እና 46 በመቶ ላይ ይገኛል።

በ2005 ዓ.ም በሰንጋ ተራ ሳይት የተጀመሩ 1292 ቤቶች ፣ በክራውን ደግሞ 5126 ቤቶች ግንባታቸው እየተፋጠነ ይገኛል ተብሏል።
 
ለቤቶቹ ግንባታ 1.5 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን ፥ በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ ዜጎች የ29.6 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር መፈጠሩንም ገልፀዋል።

ኢንተርፕራይዙ በ2007 ዓ.ም 15 ሺህ ቤቶችን በመገናኛ ፣ በኢምፔሪያል ፣ሲ ኤም ሲ፣ በቦሌ ቡልቡላና በሌሎችም አካባቢዎች ለመገንባት ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

ስራ አስኪያጁ በመግለጫቸው የመሰረተ ልማት ችግር ፣ የመሬት አቅርቦት እንዲሁም የተቋራጮች የአቅም ውስንነት በክፍተትነት አንስተዋል።

ለ40 /60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች 164 ሺህ 79 ሰዎች ተመዝግበው 2.5 ቢሊዮን ብር ቆጥበዋል።

በትዕግስት ስለሺ

አዲስ አበባ ፣ግንቦት 8፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአለም የጤና ድርጅት በ2014 ሪፖርቱ በሁሉም ስፍራ በህይወት የመቆየት ጊዜ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁሟል።

በተለይም በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ለውጡ ከፍተኛ መሆኑን ያመለከተው ሪፖርቱ ፥ በህይወት የመቆየት ጊዜ እ.ኤ.አ  ከ1990 እስከ 2012 ድረስ በአማካይ የዘጠኝ አመት እድገት ማሳየቱን ገልጿል።

በዚህም ኢትዮጵያ ላይቤሪያን ተከትላ በህይወት የመቆየት ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እድገት ከታየባቸው ስድስት ሀገራት በሁለተኛነት ተቀምጣለች።

ኢትዮጵያ በህይወት የመቆየት እድሜን ከ45 ወደ 64 በማሳደግ ነው በሁለተኝነት ደረጃ ላይ የተቀመጠችው።

የአለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ማርጋሬት ቻን ፤ በአለም አቀፍ ደረጃ በህይወት የመቆየት ጊዜ እድገት ሊያሳይ የቻለው ፥ እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህፃናትን ሞት መቀነስ በማቻሉ ነው ብለዋል።

እ.ኤ.አ በ2012 የተወለዱ ሴቶች በአማካይ 73 አመት የመኖር እድል ሲኖራቸው ፤ በአንፃሩ የወንዶች ዕድሜ 68 ገደማ ነው።
በብዙ አገራት እየቀነሰ የሚገኘው ትምባሆን የመጠቀም ልምድ መቀነስ በህይወት የመቆየት ጊዜ እንዲጨምር አስተዋፅኦ ማድረጉንም ነው ድርጅቱ ጨምሮ የጠቆመው።
ከሳህራ በታች ባሉ አገራት ማለትም በአንጎላ ፣ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በአይቮሪኮስት ፣ በሌሴቶ፣ በሞዛምቢክ እና በሴራሊዬን  በህይወት የመቆየት ጊዜ እስካሁን ከ55 መዝለል እንዳለቻለ ዘገባው ጨምሮ ገልጿል።

ምንጭ፦un.org
  

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 7፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) የአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ወደ ኢንስትቱዩነት  እንዲያድግ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

የአማኑኤል  የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሀገረ አቀፍ ደረጃ በመስኩ ህክምና በመስጠት ብቸኛው ነው።

በዚህም 270 የሚጠጉ ህሙማንን አስተኝቶ እንዲሁም ከ 600 ከፍ የሚሉትን ደግሞ የተመላላሽ የአዕምሮ ህክምና እየሰጠ ነው የሚገኘው።

የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ዳዊት  አሰፋ ሆስፒታሉ የበለጠ እንዲጠናከር እና የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ረቂቅ አዋጁ የሆስፒታሉን አግልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ስልጠናን ጨምሮ  የምርምር እና የልህቀት ማዕከል እንዲሆን የሚያስችለው ነው።

የሚሰጠውን የአዕምሮ ጤና አገልግሎት አቀናጅቶ የመምራት፤  በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሙያዎችን በብዛትና በጥራት ማፍራት ብሎም ለህክምናው መሻሻል የሚረዱ ግብአቶችን መፍጠር የሚሉ ተጠቃሾች እንደሆኑም ነው  ዶክተር ዳዊት የጠቀሱት።

 ቀደም ሲል ሆስፒታሉ  የስልጠናና የምርምር ስራዎችን በማካሄዱ ረገድ  ውስንነቶች አሉበት የሚሉት ስራ አስኪያጁ ፥ ይህ ደግሞ ረቂቅ አዋጁ ጸድቆ ስራ ላይ ሲወል መፍትሄ ያገኛል ብለዋል።


ያነጋገርናቸው የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሜዲካል ሰርቪስ ሃላፊ ዶክተር ብርቄ አንበሴ እና የየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካለ ኮሌጅ የሆስፒታሉ ዋና ፕሮቮስት ዶክተር ከተማ ድሪባ ኢንስትተየቱ በአዋጅ ጸድቆ ወደ ተግባር ሲሸጋገር ዘረፈ በዙ አገልግሎቶችን ለመስጠት እንደሚያሰችለው ነው የገለፁት።

ዶክተር ዳዊት ረቂቁን የማዘጋጀቱ ስራ እየተጠናቀቀ መሆኑና በቀጣይ ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደሚላክ አስታውሰዋል።

በአሁን ጊዜ የመጨረሻ ውሳኔ ባያገኝም  አዋጁ ከጸደቀ በኋላ የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስሙ የኢትዮዽያ አዕምሮ ጤና ኢንስቲተየት ይሆናል ተብሎ ነው የሚታሰበው።

ኢንስቲትዩቱ መቀመጫውን የሚያደርግበት ኮተቤ አካባቢ የሚገኘው የአዲሱ ህንጻ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሊጠናቀቅም የ4 ወራት እድሜ ብቻ ይቀረዋል ነው ያሉት የአማኑኤል ስፔፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ዳዊት አሰፋ።

በጥላሁን ካሳ