ደቡብ ሱዳን የፕሬዚዳንቱን የስልጣን ዘመን እስከ ፈረንጆቹ 2021 አራዘመች

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 05፣2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ሱዳን ምክርቤት የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የስልጣን ዘመን እስከ ፈረንጆቹ 2021 ማራዘሙ ተገልጿል።

የፕሬዚዳንቱን የስልጣን መራዘም የሀገሪቱ ምክር ቤት ያጸደቀ ሲሆን፥ ክስተቱ ተቃዋሚዎችን በማስቆጣት የሰላም ድርድሩን ወደ ግጭት ሊቀይረው ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።

የህግ አውጪው ክፍል አካል የሆኑት አቴም ጋራንግ ፕሬዚዳንት ኪር በዚሁ ጉዳይ ላይ ዛሬ ከሰዓት ወይንም በነገው ዕለት የፊርማ ስነስርዓት እንደሚኖራቸው ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ ከፈረንጆቹ 1994 ጀምሮ የተከሰተው ቀውስ በ10 ሺህ ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞትና ስደት ምክንያት ቢሆንም መንግስት ሀገራዊ ምርጫውን እንዲዘገይ መወሰኑ ነው የተገለጸው።

የፕሬዚዳንቱ የስልጣን ዘመን መራዘም እውን የሆነው የሀገሪቱ መንግስት ከተቃዋሚዎች ጋር ሰላማዊ ድርድር ሲደርግ ከቆየ ከቀናት በኋላ መሆኑንም ዘገባው አስታውሷል።

የተቃዋሚዎች ቃል አቀባይ ማቢኦር ጋራነግ የሰላማዊ ድርድር በጀመርንበት ወቅት መንግስት ይህን ውሳኔ መወሰኑ ወደ ቀድሞው ግጭት እንድንገባ የሚያደርግ ነው ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጻቸውን ዘገባው ያስረዳል።

 

ምንጭ፦ abcnews.go.com 

የተተረጎመውና የተጫነው፦ በእንቻለው ታደሰ