ጠ/ሚ ዶክተር አብይ ባለፉት መቶ ቀናት የህብረተሰቡን የለውጥ ፍላጎት ማሳካት የሚያስችል እንቅስቃሴ አድርገዋል - መንግስት

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 4 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፉት መቶ ቀናት የህብረተሰቡን የለውጥ ፍላጎት ማሳካት የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች ማድረጋቸውን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሀላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ።

ሀላፊ ሚኒስትሩ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ያለፉት መቶ ቀናት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህብረተሰቡን የለውጥ ፍላጎት በመገንዘብ በርካታ ስራዎችን ያከናወኑበት መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባከናወኗቸው ስራዎችም ባለፉት 100 ቀናት በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውንም ነው የተናገሩት።

በዚህም የህብረተሰቡን የለውጥ ፍላጎት ለማሳካትና ህብረተሰቡን በብቃት መምራት የሚያስችል ሰፊ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋልም ነው ያሉት።

በነበረው እንቅስቃሴም በሃገር ውስጥም ሆነ በጎረቤት ሃገራት በርካታ አመርቂ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው ህብረተሰቡም የለውጥ ተስፋና እንቅስቃሴ የተመለከተበት እንደነበር ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት መቶ ቀናቶች ከህብረተሰቡ ጋር ሰፋፊ መድረኮችን በማዘጋጀትና ቀጥታ ግንኙነት በመፍጠር ህብረተሰቡን ማወያየታቸውንም ሃላፊ ሚኒስትሩ አንስተዋል።

በዚህም የህብረተሰቡን ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠትና ሃገራዊ አንድነትን በማጠናከር ብሄራዊ መግባባትን መፍጠር የሚያስችሉ ስራዎች ተከናውነዋልም ብለዋል።

በዚህ ረገድ በተሰራ ስራም በሃገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ ግጭቶችና ውጥረቶች ረገብ እንዲሉና በህዝቦች መካከል መተማመን እንዲፈጠር አድርጓልም ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእነዚህ ቀናት የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታውን የሚያጠናክርና የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያሰፉ በርካታ ተግባራት መከወናቸውንም ሃለፊ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

ከዚህ አኳያም በተለያየ ምክንያት የታሰሩ እስረኞችን እንዲፈቱ በማድረግና ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመወያየት የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠር መስራታቸውንም አስታውሰዋል።

ከዚህ ባለፈም መቀመጫቸውን ከሃገር ውጭ ያደረጉና በትጥቅ ትግል ይንቀሳቀሱ የነበሩ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመጥራት፥ በሃገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ መጥራታቸውንም አውስተዋል።

በዚህም የሃገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር በማስፋት የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታውን ማጠናከር የሚያስችል ስራዎች መሰራታቸውንም አስረድተዋል።

በተጨማሪም በሃገር ውስጥ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ማድረጋቸውንም አንስተዋል ሃላፊ ሚኒስትሩ።

ከጎረቤትና ከተለያዩ ሃገራት ጋርም ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መፍጠር የሚያስችል ስራ መስራታቸውንም ጠቁመዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሃገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በማጠናከር ተጠቃሚነቷን የሚያሳድጉ ግንኙነቶችችን መፍጠርም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የ100 ቀናት ቆይታ ውጤት መሆኑንም ነው የገለጹት።

ከዚህ ባሻገር ከጎረቤት ኤርትራ ጋር የነበረውን ጦርነት በማስቆምና ተቋርጦ የቆየውን ግንኙነት ዳግም በማስጀመር ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ማስመዝገባቸውንም ተናግረዋል።

 


በዙፋን ካሳሁን