የኢትዮጵያና የእስራኤል የጤና ሚኒስትሮች በጋራ ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያና የእስራኤል የጤና ሚስትሮች በጋራ ለመስራት መስማማታቸው ተገለጸ፡፡

ይህ የተሰማው የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በእስራኤል አምባሳደር የተመራውን የልዑካን ቡድን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡

በእስራኤል አምባሳደር የተመራው ልዑካን ቡድን በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የጤና አገልግ ሎት በተለይም በድንገተኛ አደጋ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በአቤት ሆስፒታል፣ በእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች አምቡላንስ አገልግሎት እና በብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ያለውን አሰራር ጎብኝተዋል፡፡

ጉብኝታቸውን ተከትሎም በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የተመለከቷቸውን ክፍተቶችን ለመሙላትና አሰራሩን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ እንዲሁም የሰው ኃይል ስልጠና በጋራ የሚሰጡበትን ሁኔታ በማስቀመጥ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ መግለጻቸውን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡