አሜሪካና ጀርመን አዲስ የቃላት ጦርነት ጀምረዋል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሩሲያ ጀርመን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ የምታሳድር ሀገር ነች ብለዋል፡፡

ፕሬዚደንት ትራምፕ ይህንን ያሉት በብሩሴልስ በሚካሄደው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጉባኤ ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ጀርመን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ በሩሲያ ቁጥጥር ስር ወድቃለች ይህ ደግሞ ለኔቶ አባል ሀገራት መልካም አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በበኩላቸው ሀገራቸው ነጻ ሀገር መሆኗን ጠቅሰው ኔቶ ውስጥ ያላቸውንም ድርሻ በሚገባ እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

ሜርኬል ሩሲያና ጀርመን ያላቸውን ታሪካዊ ዳራ በማንሳት ምስራቅ ጀርመን በሶቬት ህብረት አገዛዝ ስር ነበረች ነገር ግን አሁን ያለማንም ጣልቃ ገብነት በራሷ የምትደዳር የራሷን ውሳኔ የምትወስን ሀገር ነች ብለዋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች ካናዳ የቡድን ሰባት ጉባኤ ላይ ተገናኝተው የነበረ ሲሆን በንግድ ጉዳይ ላይ መወዛገባቸው የሚታወስ ነው፡፡
ፕሬዚደንት ትራምፕ ሀገራቸው በአውሮፓ ሀገራት የተለየ ጥቅም ሲያገኙ እንደነበረ ገልጸዋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ታዲያ የአውሮፓ ህብረት የካውንስሎች ፕሬዚደንት ዶናልድ ተስክ ትራምፕ በየዕለቱ በትዊተር መልዕክታቸው አውሮፓን መውቀስ ማቆም አለባቸው ብለዋል፡፡

በቅርቡ የአውሮፓ ህብረት ባወጣው መረጃ ጀርመን ከ50 በመቶ እስከ 75 በመቶ የሚደርሰውን የነዳጅ ሃይል የምታገኘው ከሩሲያ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ትራምፕ የኔቶ ገባዔ እንዳጠናቀቁ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በፊኒላንድ ቆይታ ከማድረጋቸው ቀደም ብሎ ወደ ብሪታንያ በመዝለቅ ለአራት ቀናት ያህል ቆይታ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡

 

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ
በአብርሃም ፈቀደ