አሜሪካ 200 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ባላቸው የቻይና ምርቶች ላይ ቀረጥ ልትጥል ነው

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 4 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ በቻይና ምርቶች ላይ ተጨማሪ ቀረጥ ልትጥል መሆኑን አስታወቀች።

እስከ መስከረም ወር ድረስ ይተገበራል የተባለው አዲሱ ቀረጥ 200 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ባላቸውና ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የሚጣል ነው ተብሏል።

በዚህም መሰረት ከ6 ሺህ በላይ የቻይና ምርቶች እስከ 10 በመቶ ቀረጥ ይጣልባቸዋል ነው የተባለው።

ምግብና የማዕድን ውጤቶችን ጨምሮ የተለያዩ የፍጆታ እቃዎችም አዲሱ የአሜሪካ ቀረጥ ይመከታቸዋል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቻይና አሜሪካ ለምትጥለው ቀረጥ ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ምላሽ የምትሰጥ ከሆነ፥ ተጨማሪ ቀረጥ እንደሚጣልባት ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።

ከዚህ ባለፈም ከባለቤትነት መብት ጋር በተያያዘ የአሜሪካ የሆኑ ምርቶችን ቻይናውያን ኩባንያዎች በህገ ወጥ መልኩ በባለቤትነት መጠቀማቸው ለእርምጃው ምክንያት መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።

ይህን ተከትሎም 200 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያላቸው የቻይና ምርቶች ከመስከረም ወር ጀምሮ ቀረጥ ይጣልባቸዋል ነው የተባለው።

ዋሽንግተን በዚህ ወር ደግሞ 16 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ባላቸው የቻይና ምርቶች ላይ ተጨማሪ ቀረጥ እንደምትጥል ገልጻለች።

ሁለቱ ሃገራት ባለፈው ሳምንት አንዳቸው በአንዳቸው ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ቀረጥ መጣል መጀመራቸው ይታወሳል።

አሜሪካም ሆነች ቻይና 34 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ባላቸው የየሃገራቱ ምርቶች ላይ ቀረጥ በመጣል ወደ ንግድ ፍጥጫ ገብተዋል።

ይህ ቀረጥ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ያለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮም፥ የእስያ የአክሲዮን ገበያ ክፉኛ ማሽቆልቆሉ ተነግሯል።

አሁን ባለው የአክሲዮን ገበያ በሆንግ ኮንግ፣ ሻንጋይ እና ጃፓን ከ1 ነጥብ 7 እስከ 2 በመቶ መውረዱም ተሰምቷል።

 

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ