በአፋር ክልል ዲቾቶ ከተማ ሁለት የነዳጅ ቦቴዎች ተጋጭተው በደረሰው የእሳት አደጋ ሁለት ንግድ ባንኮች ሙሉ በሙሉ ወደሙ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2010 (ኤፍቢሲ) በአፋር ክልል ዞን አንድ ኤልዲሃር ወረዳ ዲቾቶ ከተማ ዛሬ ቀን 8 ሰዓት ላይ ሁለት የነዳጅ ቦቴዎች ተጋጭተው በተቀሰቀሰ የእሳት አደጋ በአቅራቢያቸው በነበሩ ህንፃዎች ላይ ጉዳት ደረሰ።

የከተማዋ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ሻምበል ዑስማን መሀመድ አሊ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት፥ ከጅቡቲ የአውሮፕላን ነዳጅ ጭኖ የሚመጣ ቦቴ ከሌላ የነዳጅ ቦቴ ጋር በመጋጨቱ ነው የእሳት አደጋው የደረሰው።

ቦቴዎቹም ፈንድተው የተቀሰቀሰው እሳት በአቅራቢያቸው የነበሩ የኢትዮጵያ እና የአንበሳ ንግድ ባንኮች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።

በተጨማሪም ሌሎች በአከባቢው ያሉ የንግድ እና መኖሪያ ቤቶች በእሳት የተያያዙ ሲሆን፥ እሳቱን በቁጥጥር ሰር ለማዋል ጥረት እየደረገ መሆኑን አዛዡ ተናግረዋል።

የቦቴዎቹ አሽከርካሪዎች በአሁኑ ሰዓት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየደረገባቸው መሆኑንም ነው ያስታወቁት።

 

በታሪክ አዱኛ