በዝንባብዌ በፈረንጆቹ ሀምሌ 30 ለሚካሄደው ምርጫ የተወዳዳሪዎች ምዝገባ ተጀምሯል

አዲስ አበባ ሰኔ7፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ) በዝንባብዌ በፈረንጆቹ የፊታችን ሀምሌ 30 ለሚካሄደው ምርጫ የተወዳዳሪዎች ምዝገባ በሳለፍነው ሀሙስ መጀመሩ ተገልጿል። 

በዚሁ ምርጫ መራጮች በአገር አቀፍ ደረጃ በተመሳሳይ ቀን በሚሰጡት ድምጽ ተወዳደሪዎቹ በእየደረጃው በሀገሪቱ በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች በተሰጠው የድምጽ ድምር ውጤት አሸናፊዎቹ እንደሚለዩ ነው የተገለጸው።

 ከሙጋቤ የረጅም የፕሬዚዳንት ስልጣን ዘመን በኋላ በትረ ስልጣኑን የተረከቡት ፕሬዚዳንት ኢመርሰን ምናንጋግዋ በዚህ ምርጫ ለመወዳደር ከተመዘገቡት ተወዳዳሪዎች አንዱ ሲሆኑ፥ በምርጫው ያሸንፋሉ ተብሎ ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው ተወዳዳሪዎች ቀዳሚው ናቸው ተብሏል።

ኮረኮዳይል የሚል ስያሜ የተሰጣቸው የ75 ዓመቱ ኢመርሰን ምናንጋግዋ በዚህ ምርጫ ካሸነፉ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ትኩረት ሰጥተው አንደሚሰሩ በመራጮች ዘንድ እምነት የተጣለባቸው መሆኑም ተገልጿል።

ፕሬዚዳነቱ ሀገራቸውን ነፃነት ለማስከበር ብርቱ ጥረት ከደረጉ ሰዎች መካከል አንዱ ሲሆኑ፥ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለእስር ተዳርገው የነበሩ መሆኑንም ነው ዘገባው የሚያስረዳው።

በዚህ ምርጫ ካሸነፉም የባህር ወደብ የሌላት ሀገራቸውን ዲፕሎማሲያው ግንኙነት ለማጠናከርና ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ እንደሚሰሩም ቃል መግባታቸው ነው የተገለጸው።

ኔልሰን ቻሚሳ የተባሉት የዴሞክራሲያው ለውጥ አብዮት ፓርቲ አባል የፕሬዚዳንት ምናንጋግዋ የቅርብ ተዎዳዳሪ ይሆናሉ ተብሎ ግምት ተሰጥቷቸዋል።

የዴሞክራሲያው ለውጥ አብዮት ፓርቲ የሰባት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት ሲሆን፥ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሊሆን ይችላል ተብሎ ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው ፓርቲዎች ይመደባል ነው የተባለው።

ቻሚሳ ፓስተር፣ የህግ ምሁርና በማህበራዊ ሚዲያ በርካታ የሀገሪቱ ወጣት ተከታዮች ያሏቸውና ተፅኖ ፈጣሪ መሆናቸውም ታውቋል ።

ቀደም ሲል በፈረንጆቹ 2003 በ25 ዓመታቸው የሀገሪቱ ፓርላማ አባልና የዴሞክራሲያው ለውጥ አብዮት ፓርቲ ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠው የነበረ መሆኑም ታውቋል።

በተጨማሪም አምብሮስ ሙቲንሂሪ የተባሉት የብሄራዊ አርበኞች ግንባር ፓርቲ ተወዳዳሪ በቅርብ ጊዜ ፖለቲካውን የተቀላቀሉና የመራጮች ትኩረትን ሊስቡ የሚችሉ ናቸው ተብሏል።

ይህ ምርጫ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሙጋቤ ያልተሳተፉበት ሲሆን፥ ኤንፒ ኤፍ ፓርቲ ከሙጋቤና ከቀድሞዋ ቀዳማዊ እመቤት ግሬስ ሙጋቤ ድጋፍ እያገኘ መሆኑ ተገልጿል።

 

ምንጭ፦ aljazeera.com

የተተረጎመውና የተጫነው፦ በእንቻለው ታደሰ