በ2009 በጀት የኦዲት ክትትል ከ173 ተቋማት 25ቱ ብቻ የኦዲት ግኝት የለባቸውም

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በ2009 በጀት የኦዲት ክትትል ከተደረገባቸው 173 ተቋማት 25ቱ ብቻ የኦዲት ግኝት የለሌለባቸው መሆኑ ተገለጸ።

በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር የኢንስፔክሽን ዳይረክተር አቶ ፈቃዱ አጎናፍር የገንዘብ ጉድለት የታየባቸው ተቋማት ወደ ፊት በህግ አግባብ የሚጠየቁና በግለሰቦች ላይም አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።

የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር በሀገሪቱ የገንዘብ አስተዳደር ና ግዢ ስርአት ዙርያ ከውስጥ ኦዲተሮች ጋር ውይይት እያደረገ ነው።

በምክክር መድረኩ የውስጥ ኦዲተሮች እርስ በእርስ ያለመስማማት፣ የሙያ ነፃነትን ያለአግባብ መጠቀም፣ የኦዲት ግኝቶችን በወቅቱ ያለማሳወቅና የመንግስት ግዥና ፋይናንስ መመሪያዎችን በትክክል የማወቅ ክፍተቶች እንዳሉባቸው ተመላክቷል።

በ112 ተቋማት የ2009 በጀት ላይ በተደረገ ክትትል ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ የአላቂ እቃ ግዥ የተፈጸመ ና በ120 ተቋማት ደግሞ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ በአላቂ ንብረቶች ፈሰስ እንካተት ተደርጓል ተብሏል።

በዚህም ተቋማቱ በጀት ከሚቃጠል በሚል በበጀት ዓመቱ መጨረሻ አካባቢ በርካታ ስልጠናዎችና ክፍያዎችን በመፈጸም ገንዘብ የሚያባክኑ መሆኑ ነው የተገለጸው።

አሁን ላይ በ2009 በጀት ዓመት የጎላ የኦዲት ግኝት ያለባቸው 61 ተቋማት ላይ ክትትሉ እየተደረገ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካክል 38 ተቋማት ት/ሚንስቴርና እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ 15ቱ የኢኮኖሚ ልማት ዘርፎችና 13ቱ የአስተዳደርና አገልግሎት ዘርፎች መሆናቸውም ታውቋል።

የኦዲት ግኝቱ በአማካሪ ድርጅቶች ትክክለኛነቱ ሳይረጋገጥ ክፍያ በመፈጸም፣ ለተለያዩ ጉዳዮች የገንዘብ ወጪ በማድረግ፣ ከውጭ ሀገር መምህራን ክፍያ ግብር ባለመቀነስ የተከሰተ መሆኑን ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት።

ከውጭ ሀገር መምህራን ገቢ ግብር ተቀናሽ ባለማድረግ ብቻ 6 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ጉድለት የተመዘገበ መሆኑም ታውቋል።

ከሳምንታት በፊት ከመንግስት መስሪያ ቤት በአግባቡ ያልተሰበሰበና ያልተወራረደ ገንዘብ መኖሩ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት መቅረቡ የሚታወስ ሲሆን ፥በዚህም 21 ቢሊየን ያህል ብር ጉድለት መታየቱን መረጃዎች አመላክተዋል።

 

በቤተልሄም ጥጋቡ