የሀገሪቱ እድገትና ትራንስፎርሜሽን አሳታፊና ዘላቂ ሊሆን እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሀገሪቱ እድገት እና ትራንስፎርሜሽን አሳታፊ እና ዘላቂ ሊሆን ይገባል ተባለ።

የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን “የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን ክትትል እና ግምገማ ፤ የትና እንዴት መለካት ይገባዋል” በሚል ርእስ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በመተባበር የጋራ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ የትራንስፎርሜሽን እቅዱ ከግል ዘርፍ አኳያና የከተማ ዘርፍ ልማትን የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በቀረቡት ፅሁፎች ውስጥ “እድገት እና ትራንስፎርሜሽን ምንድን ነው፣ እደገት ሲባልስ ምን ማለት ነው” በሚል ከኦኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ዶክተር ታደለ ፈረደ ጥናት አቅርበዋል።

በጥናታዊ ጽሁፉም ትራንፍርሜሽን 3 ነገሮች ሊኖሩት ይገባል የተባለ ሲሆን፥ ይህም ይህም የኦኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና አካባቢ ትራንስፎርሜሽን ናቸው፤ እነዚህ ሶስቱ አብረው ሲሄዱ ነው ለውጥ የሚታየው ተብሏል።

በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ መሰለፍ እና ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት ይጠበቅብናል የሚለውም በፅሁፉ ቀርቧል።

ከዚህ አንፃር የመጀመሪያው የእቅድ ዘመን ተጠናቆ ሁለተኛውን ቢጋመስም፤ በዚህም የተመዘገቡ ለውጦች ቢኖሩንም በቂ እንዳልሆኑም ተገልጿል።

በግብርናው ላይ የምርት መጠን ጨምሯል ሆኖም ግን በቂ አይደለም የተባለ ሲሆን፥ የወጪ ንግድ አፈፃፀም በሀለቱም የእቅድ ዘመኖች ማሻሻል እንዳልተቻለም በመድረኩ ተነስቷል።

እንዲሁም ስራ እድልን በተመለከተም በእቅድ ዘመኖ በሚፈለገው ደረጃ የስራ እድል መፍጠር እንዳልተቻለም ተነስቷል።

ከውጭ ምንዛሬ አኳያም በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አጋማሽ የተገኘው የውጭ ምንዛሬ አነስተኛ መሆኑ እና የውጭ ምንዛሬ ለማድረግ የሚደረገው ጥረትም ዝቅተኛ መሆኑ ተገልጿል።

በአጠቃላይ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ግምገማው በመንግስት ብቻ ሳይሆን ገለግተኛ በሆኑ ተቋማትም ሊገመገም እንደሚገባም ተመልክቷል።

በተመስገን እንዳለ