የሐብሊ ማእከላዊ ኮሚቴ ባሳለፍነው ቅዳሜ በሀረር ከተማ ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት አወገዘ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሐረሪ ብሄራዊ ሊግ (ሐብሊ) ማእከላዊ ኮሚቴ ባሳለፍነው ቅዳሜ ሰኔ 02 ቀን 2010 ዓ.ም የተፈጠረውን ግጭት በፅኑ አወገዘ።

የሐብሊ ማእከላዊ ኮሚቴ ለሶስት ቀናት ያደረገውን ግምገማ ተከትሎ የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫውም ሰኔ 02 2010 ዓ.ም በሀረር ከተማ በተቀሰቀሰ ግጭት በሰው ላይ የአካል መቁሰልና የስነ ልቦና እንዲሁም በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን በማንሳት ይህንንም እንደሚያወግዝ አስታውቋል።

ድርጊቱም ሐብሊን እና ኦህዴድን አይወክልም ያለው ማዕከላዊ ኮሚቴው፥ ድርጊቱ የፀረ ሰላም ሀይሎች እንቅስቃሴ መሆኑንና አጥፊዎችን በህግ መጠየቅ እንዳለባቸው ገልጿል።

በዚህ ጥፋት የደረሰውን ጉዳት መንግስትና ህዝብ ተባብረው እንዲሚያካክሱ ማእከላዊ ኮሚቴው አቅጣጫ ማስቀመጡም በመግለጫው ተመልክቷል።

በሀረር ከተማ የተፈጠረውን ሁከት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ጥቂት ግለሰቦች የግል ፍላጎታቸውን ለማራመድ ከጀመሩት ህገ ወጥ እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ ማእከላዊ ኮሚቴው በመግለጫው አሳስቧል።

በተጨማሪም ማእከላዊ ኮሚቴው የድርጅቱ ሊቀመንበር ያቀረቡትን የመልቀቂያ ጥያቄ በመርህ ደረጃ ችግር የሌለበት መሆኑን መገምገሙም ተገልጿል።

የመልቀቂያ ጥያቄውን ተከትሎ ሰላማዊ ስልጣን ሽግግር እንዲኖር ሁኔታዎችን በማመቻቸት በሂደት ተግባራዊ እንዲሆን አቅጣጫ ማስቀመጡን ከሀረሪ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።