የቦንጋ ብሄራዊ የቡና ሙዚየም በ2007 ተመርቆ ቢከፈትም እስካሁን ወደ ስራ አልገባም

አዲስአበባ፣ ሰኔ 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ክልል የቦንጋ ብሄራዊ የቡና ሙዚየም ግንባታው ከሶስት ዓመታት በፊት ቢጠናቀቅም የሚያስተዳድረው አጥቶ እስካሁን ወደ ስራ አልገባም ተባለ።

በ35 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው ሙዚየም የፌዴራል ወይስ የክልል መንግስት ያስተዳድረው የሚለውን ለመወሰን የሚያስችል የህግ ማዕቀፍም እንዳልተዘጋጀለት ተገልጿል።

ጉዳዩ የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣንንም እያወዛገበ ነው ተብሏል።

ሙዚየም በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በ2007 ዓመተ ምህረት ተመርቆ መከፈቱ ይታወሳል።

ከተመረቀ በኋላ ወደ ስራ መግባት ተሳነው ሙዚየሙ፤ ማን ያስተዳድረው የሚለው ጉዳይ እስካሁን እልባት ባለማግኘቱ ነው ችግሩ የተፈጠረው ይላሉ የክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ  ምክትል ሀላፊ አቶ አቡቶ ሀሚስ።

አቶ አቡቶ ራሱን የቻለ አደረጃጀት ለመፍጠር የህግ ማዕቀፍ መዘጋጀት ስላለበት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ኃላፊነቱን ወስዶ በፍጥነት ስራውን ሊያጠናቅቅ ይገባል የፌዴራል መንግስት የማያስተዳድረው ከሆነም ክልሉ የራሱን ስራ ይቀጥላል ብለዋል።

በተጨማሪም የሙዚየሙ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት የባለድርሻ አካላት ሚና በግልፅ ያልተቀመጠ ሲሆን፥ ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላም እንዲሁ ተገቢው ስራ አልተሰራም ብለዋል።

ብሄራዊ የቡና ሙዚየሙ በ2007 ሲመረቅ አደረጃጀቱ በፍጥነት እንዲሰራ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

በወቅቱ ለተለያዩ አካላት የስራ ኃላፊነት ሲሰጥ ተሳታፊ የነበሩት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ፤ ከክልሉ߹ ከዞን እና ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጣ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰዋል።

ባለስልጣኑ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ለማገዝ የቡና ሙዚየሙ አደረጃጀት ምን መምሰል እንዳለበት የሚወስን ረቂቅ የህግ ማዕቀፍ ከ2007 ጀምሮ ሲያዘጋጅ እና ለሚኒስቴሩ ሲያቀርብ ቆይቷል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ ይሁን እንጂ ሚኒስቴሩ ረቂቁን በማጠናቀቅ ረገድ ክፍተት እንዳለበት ጠቁመዋል።

በያዝነው ዓመት መጀመሪያም ረቂቅ የህግ ማዕቀፉን በድጋሚ በመከለስ ብንልክም ሚኒስቴሩ እስካሁን ህጉን ያለማጽደቁን አቶ ዮናስ ገልጸዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት አቶ በላቸው ድሪባ ባለስልጣኑ የላከው የህግ ማዕቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ባለመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

ሰነዱ የቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለስልጣን በተቋቋመበት አዋጅ አይነት የተዘጋጀ ቢሆንም በሀገሪቱ ካለው የተቋም አመሰራረት ጋር ተያይዞ የሚጣጣም አይደለም ይላሉ ዳይሬክተሩ።

አቶ በላቸው የህግ ማዕቀፉ ለማዘጋጀት ጊዜ ሊወስድ የቻለው የቡና ሙዚየሙን በተመለከተ ውይይት የተደረገው በበላይ አመራሮች ብቻ ነው የሚሉት አቶ በላቸው፤ ይህም ባለሙያዎች በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ እንዳይኖራቸው ማድረጉን ይናገራሉ።

በዚህም የሚኒስቴሩ የህግ ክፍል ከሙዚየሙ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች ላይ የተሟላ እይታ እንዳይኖረው ችግር ፈጥሯል ይላሉ።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተዘጋጀው የህግ ማዕቀፍ ችግር ያለበት መሆኑን ከተረዳ በኋላ ኮሚቴ አዋቅሮ ወደ ስራ ገብቷል።

ኮሚቴው ረቂቅ ብሄራዊ የቡና ሙዚየም አወቃቀር ደንብ ሲያዘጋጅ ቆይቶም ባለፈው መጋቢት ወር ማጠናቀቁን ገልጸዋል።
ረቂቁ ለሚኒስቴሩ የበላይ አመራሮች መቅረቡንና ከባለድርሻ አካላት ጋር ከተመከረበት በኋላም ለሚመለከተው አካል እንደሚላክ አቶ በላቸው ተናግረዋል።

በቀጣዩ ዓመትም ህጉ ፀድቆ ሙዚየሙ ወደ ስራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ያም ሆነ ይህ ግን በህዝብ ሀብት የተገነባው ሙዚየም በተቋማት ያለመናበብ እና ኃላፊነት ያለመወጣት ባለቤት አልባ ሆኖ ቀጥሏል።

 

 

በፋሲካው ታደሰ