ኢራን የኒውክሌር ስምምነቱ የማይከበር ከሆነ ዩራኒየም ማበልጸጓን እንደምትጀምር አስጠነቀቀች

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢራን ከሃያላን ሃገራት ጋር የገባችው የኒውክሌር ስምምነት የማይከበር ከሆነ ዩራኒየም ማበልጸጓን እንደምትጀምር አስጠነቀቀች።

ቴህራን በፈረንጆቹ 2015 ከሃያላን ሃገራት ጋር የገባችው የኒውክሌር ስምምነት የማይከበር ከሆነ፥ በፎርዶው እና ናታንዝ የኒውክሌር ማበልፀጊያ ማዕከሎቸ ዩራኒየም ማበልጸጌን እጀምራለሁ ብላለች።

የኢራን አቶሚክ ሃይል ቃል አቀባይ ቤህሩዝ ኻማልቫንዲ እንዳሉት በኒውክሌር ማበልጸጊያ ማዕከሎቹ አዲስ ስራ ሊጀመር እንደሚችል ተናግረዋል።

እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ ዩራኒየም የማበልጸጉ ስራ የሃገሪቱ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒን ትዕዛዝ ተከትሎ የሚጀመር ነው።

መንፈሳዊ መሪው ይጀመራል የተባለው ስራ ኢራን ከሃያላኑ ጋር የገባችውን ስምምነት መርህ በጠበቀ መልኩ የሚከናወን እንዲሆን ትዕዛዝ መስጠታቸውንም ተናግረዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ናታንዝ በተባለው የኒውክሌር ማበልፀጊያ ማዕከል አዳዲስ የኒውክሌር መሳሪያዎች እንደሚተከሉም ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ አሊ ኻሚኒ የማበልጸግ ስራው ይጀመር የሚል ትዕዛዝ ካስተላለፉ ቴህራን በድጋሚ ኒውክሌር ማበልጸጓን ትቀጥላለችም ነው ያሉት።

የኢራን አቶሚክ ሃይል ሃላፊ አሊ አክባር ሳልህ በበኩላቸው፥ በናታንዝ ኒውክሌር ማበልፀጊያ ማዕከል ቁሳቁስ የማሟላት ስራ መጀመሩን ተናግረው ነበር።

የአሁኑ የኢራን ማስጠንቀቂያ ከአሜሪካ ውጭ በስምምነቱ ውስጥ የቀሩት ሃገራት የገቡትን ስምምነት ጠብቀው እንዲቆዩ ለማድረግ ያለመ መሆኑም ተነግሯል።

አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ጀርመን፣ ብሪታንያ፣ ቻይና እና ፈረንሳይ በፈረንጆቹ 2015 ከኢራን ጋር የኒውክሌር ስምምነት መግባታቸው ይታወሳል።

ስምምነቱ ኢራን ኒውክሌር ማበልጸጓን እንድታቆምና ኒውክሌሩንም ለሰላማዊ ግልጋሎት እንድታውለው የሚያደርግ ሲሆን፥ በአንጻሩ ቴህራን በአሜሪካና አጋሮቿ የተጣላባት ማዕቀብ የሚነሳላት ይሆናል።

ለዚህ ደግሞ ሃገራቱ ኢራን በ10 አመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ከኒውክሌር ማበልጸጓ እንድትወጣ ጊዜ ሰጥተዋታል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን ይህ አካሄድ ኢራን በድብቅ ኒውክሌር ማበልፀጓን እንድትቀጥል እድል ይሰጣታል በሚል ሃገራቸውን ከስምምነቱ አስወጥተዋታል።

ሌሎች አምስት ሃገራት ግን አሁንም የተደረሰው ስምምነት እንዲከበር እየሰሩ መሆኑን ሲገልጹ ቆይተዋል።

ኢራን በበኩሏ አሜሪካና አጋሮቿ በኒውክሌር ማበልጸግ ሰበብ እስራኤልን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰሩ ነው ስትል ትኮንናለች።

እንደ ቴህራን ገለጻ የእነ አሜሪካ አላማ ኢራንን በማዳከም እስራኤልን በኒውክሌር ጦር ማጠናከር ነው።

ቴህራን እስራኤል ያለ እነ አሜሪካ ድጋፍ በጭራሽ ኒውክሌር ልትታጠቅ እንደማትችልም ትገልጻለች።

 

 

 


ምንጭ፦ ሬውተርስ