አሜሪካ በኖርዌይ ተጨማሪ የባህር ሃይል ልታሰፍር ነው

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ በኖርዌይ ተጨማሪ የባህር ሃይል አባላቷን ልታሰፍር ነው።

የኖርዌይ መንግስትም አሜሪካ ወደ ስፍራው ተጨማሪ 400 የባህር ሃይል ለማስፈር ያቀረበችውን ሃሳብ አፅድቆታል።

ይህን ተከትሎም አሜሪካ በኖርዌይ የምታሰፍረው የባህር ሃይል ቁጥር 700 የሚደርስ ይሆናል።

ሩሲያ በፈረንጆቹ 2014 ክሬሚያን ከያዘች በኋላ ዋሽንግተን እና ሞስኮ በስፍራው ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል።

ይህን ተከትሎም አሜሪካ ባለፈው አመት በፈረቃ የሚንቀሳቀሱ 300 የባህር ሃይል አባላቷን በኖርዌይ ቫኤርነስ አስፍራ ቆይታለች።

አሁን ላይም 400 ተጨማሪ የባህር ሃይል የምትልክ ሲሆን፥ የባህር ሃይሉ ሰተርሞኤን በተባለ አካባቢ ይሰፍራል ነው የተባለው።

የፔንታገን ቃል አቀባይ የሆኑት ኤሪክ ፋኦን እንዳሉት የባህር ሃይሉ በኖርዌይ በስልጠና እና ቅኝት በማድረግ የሚቆይ ይሆናል።

የባህር ሃይሉ በድንበር አካባቢ በሚገኝ ተራራማ ስፍራዎች ልምዱን ያደርጋል።

ልምምዱም የሃገራቱን ወታደራዊ ትብብሮሽ በማጠናከር ግጭት በሚፈጠር ወቅት ምላሽ ለመስጠት ያስችላልም ነው ያሉት።

ኖርዌይ በሃገሯ የአሜሪካ ባህር ሃይል እንዲሰፍር መፍቀዷ ግን በሞስኮ ዘንድ በበጎ ጎኑ አልታየም።

ጉዳዩን የሚከታተሉ ታዛቢዎችም ይህ ውሳኔ ኖርዌይን የሩሲያ ኢላማ ሊያደርጋት ይችላል በሚል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ኖርዌይ ከሩሲያ ጋር 196 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ድንበር ትጋራለች።

 

 

 

ምንጭ፦ ሲ ኤን ኤን