የሲዳማ ብሄር የዘመን መለወጫ ፊቼ ጨምበላላ ተከበረ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሲዳማ ብሄር የዘመን መለወጫ ፊቼ ጨምበላላ በዓል በተለያዩ ስነ ስርዓቶች በድምቀት ተከበረ።

ትናንት በሀዋሳ ከተማ መከበር የጀመረው የሲዳማ ብሄር የዘመን መለወጫ ፊቼ ጨምበላላ በዓል ዛሬም በተለያዩ ስነ ስርዓቶች በደማቅ ስነ ስርዓት ተከብሯል።።

በሲዳማ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች የተውጣጡ የሃገር ሽማግሌዎች በበዓሉ ላይ “የቄጣላ” ጨዋታና የፈረስ ጉግስን ጨምሮ የተለያዩ ዝግጅቶችን አከናውነዋል።

በበዓሉ ላይ የተገኙት የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ፥ ፊቼ ጨምበላላ የሰላም፣ የፍቅር እና የአንድነት በዓል መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻርም ይህን የበዓሉን እሴት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

ርዕሰ መስተዳድሩ አባቶች በዓሉን አቆይተው ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ በማድረጋቸው ሊመሰገኑ እንደሚገባቸው አንስተዋል።

ወጣቱ ትውልድም ከአባቶች የተረከበውን ድንቅ በዓል ሳይበረዝ የመጠበቅና የማስቀጠል ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን በበኩላቸው፥ ይህን በዓል ጠብቀው እዚህ ላደረሱ አባቶች ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

የፊቼ ጨምበላላ በዓል በመንግስታቱ ድርጅት የሳይንስ፣ ትምህርትና ባህል ማዕከል (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡን ጠቅሰው፥ ይህን ታሪካዊነት ማስቀጠል ይገባልም ነው ያሉት።

ሚኒስትሯ የሃገሪቱን የተለያዩ ታሪካዊ ቅርሶች እና ባህል በአለም አቀፉ መድረክ ለማስተዋወቅና ለማስመዝገብ የተደረጉ ጥረቶች ስኬታማ እንደነበሩም ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የሃሪቱን ባህልና ቅርሶች የማስተዋወቁና የማስመዝገቡ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በዓሉ በሲዳማ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች ለተከታታይ ሁለት ሳምንታት በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ይሆናል።


በብርሃኑ በጋሻው