ባለስልጣኑ በመዲናዋ የሚከሰተውን ጎርፍ ችግር ለመቅረፍ እንደሚሰራ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ትናንት ማምሻውን የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን እስከመግታት የደረሰ ችግር ተከስቷል።

በተለይም ከስአሊተ ምህረት አደባባይ እስከ መገናኛ ያለው መንገድ ከባድ ጎርፍ በመከሰቱ እግረኞችም ሆነ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ሌሎች የመንገድ አማራጮችን እንዲጠቀሙ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

የመዲናዋ ነዋሪዎች እየጣለ ያለው ዝናብ በዚሁ ከቀጠለ አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ይስጡበት ሲሉ ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ከፋና ብሮድካስቲነግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ የአዲስ አበባን መንገዶች ምቹና ዘመናዊ ለማድረግ ባለስልጣኑ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወኑን ገልፀዋል።

መንገዶቹን ምቹ ለማድረግ የሚሰራው ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያነሱት ኢንጂነር ሀብታሙ፥ ሆኖም ግን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ጊዜ የሚፈልግ ነው ብሏል።

ሰሞኑን ከባድ ዝናብ እየጣለ መሆኑን ተከትሎ በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች የትራንስፖርት እንቅስቃሴን እስከመግታት የደረሰውን ችግር ለምን መቅረፍ አልተቻለም ለተባለው፤ ዋናው ችግር የመዲናዋ አቀማመጥ ለጎርፍ የተጋለጠች መሆኑን አንስተዋል።

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋነኛ ስራው ከመንገድ ጋራ ባሉ ተፋሰሶች ላይ ነው ሆኖም ገን ጎርፉ በወንዞች ሙላት እና በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላልም ብለዋል ኢንጂነር ሀብታሙ።

ባለስልጣኑ የተፋሰስ መሄጃ መንገዶችን በወጣቶች፣ ተደራጅተው በሚንቀሳቀሱ ማህበራት እና በራስ ሀይል የማጽዳት ስራ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

አሁን ያለው ችግር ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አቅም በላይ እየሆነ መጥቷል ያሉት ኢንጂነር ሀብታሙ፥ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ በልማት ስራ ላይ የተሰማሩ አካላት እና መንግስት የተፋሰስ መሄጃ መንገዶችን ፅዳት መጠበት አለበት ብለዋል።

ዘንድሮ ክረምቱ አስቀድሞ በመግባቱ ከዚህ በኋላ ጎርፍ ሊከሰት ይችላል ያሉት ስራ አስኪያጁ ጥንቃቄ መውሰድ ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ከባድ ዝናብ እየጣለ መሆኑን ተከትሎ በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች ላይ ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ መጥለቅለቅ ችግር አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በሰው ሀይል ተደራጅቶ በተጠንቀቅ ላይ መሆኑንም አንስተዋል።