የ1997 ዓ.ም ነባር የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎች በሚቀጥለው ዓመት የቤት ባለቤት እንደሚሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የ1997 ዓመተ ምህረት ነባር የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎችን በሚቀጥለው ዓመት ሙሉ ሙሉ የቤት ባለቤት ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው የቀሩት ነባር ተመዝጋቢዎች 78 ሺህ መሆናቸውን ጠቁሞ አሁን ላይ ከ94 ሺህ በላይ ቤቶች በጥሩ የግንባታ አፈፃፀም ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ነባር ተመዝጋቢዎች በ2011 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ የቤት ባለቤት እንደሚሆኑ፥ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ይድነቃቸዉ ዋለልኝ ተናግረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በ11ኛው የቤት እጣ አወጣጥ ስነ ስርዓት ላይ የባለ ሶስት መኝታ ቤት ተመዝጋቢዎችን ሙሉ በሙሉ የቤት ባለቤት ማድረጉን መግለጹ ይታወሳል።

ሆኖም ነባር ባለ ሶስት መኝታ ቤት ተመዝጋቢዎች እጣ ወጥቶላቸዋል መባሉን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ጥያቄ ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡

በወቅቱም የቤት ባለቤት የሆኑት 29 ወር የቆጠቡ ብቻ መሆናቸውን ያነሱት ሃላፊው፥ አሁን ላይ የነባር ባለ ሶስት መኝታ ቤት ተመዘጋቢዎች የሆኑና ከ3 ወር ጀምሮ የቆጠቡ የቤት ባለቤት መሆን ችለዋል ብለዋል።

የከተማዋን ነዋሪዎች የቤት ችግር ለመፍታት አስተዳደሩ ባለፉት ጊዜያት በ11 ዙሮች ከ176 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ለተጠቃሚዎች ማስተላለፉንም ተናግረዋል።

በቀጣይም ከ132 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ በመሆኑ፥ በቅርቡ ለእድለኞች ለማስረከብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሃላፊው አያይዘውም በ2005 ዓ.ም የተመዘገቡ የቤት ፈላጊዎችን ተጠቃሚ ለማድረግም የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል።

በሌላ በኩልም መንግስት የኪራይ ቤቶች፣ የማህበር ቤቶች እና ሌሎች አማራጮችን እያቀረበ በመሆኑ የመዲናዋን ቤት ፈላጊዎች ለማርካት አጋዥ ይሆናልም ነው ያሉት።

በ2005 ዓ.ም በባለ ሶስት መኝታ ቤት የተመዘገቡ የቤት ፈላጊዎች ደግሞ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በእጣ እንደሚካተቱ ገልጸዋል።

አሁን ላይ አስተዳደሩ ቤቶችን ከስራ ተቋራጮች መረከቡን ጠቅሰው፥ በመሰረተ ልማት አለመሟላት ሳቢያ ለቤት ፈላጊዎች ማስተላለፍ አለመቻሉንም አስረድተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የመዲናዋን ነዋሪዎች ቤት ፍላጎት ለማርካት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ያነሱት ሃላፊው፥ ህብረተሰቡ የሚጠበቅበትን ቁጠባ እንዲያካሂድም ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ ይድነቃቸው በአጠቃላይ ከቤት ፈላጊው ከ20 ቢሊየን ብር በላይ መቆጠቡንም ነው ያነሱት።

 

 

 

በተመስገን እንዳለ