ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ የግብጽ ቆይታቸውን አጠናቀው አዲስ አበባ ገቡ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 4 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የግብጽ ቆይታቸውን አጠናቀው አዲስ አበባ ገቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሁለት ቀናት ያደረጉትን የግብጽ ቆይታ አጠናቀው ዛሬ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በግብጽ በተለያየ ምክንያት ታስረው የነበሩ ኢትዮጵያውያን አብረው አዲስ አበባ ገብተዋል።

ወደ ሃገራቸው የተመለሱት እስረኞች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲ ሲ ጋር ባደረጉት ውይይት ከእስር እንዲለቀቁ በተወሰነው መሰረት ከእስር የተለቀቁ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በግብጽ ቆይታቸው ከግብጹ አቻቸው አብዱል ፈታ አል ሲ ሲ ጋር በሁለትዮሽና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ሃገራቱ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሁለቱን ሃገራት የመልማት ፍላጎት ባከበረ መልኩ በአዲስ መንፈስ በጋራ ለመስራትም ተስማምተዋል።

መሪዎቹ ሁለቱ ሃገራት በተለያዩ መስኮች በተለይም በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም ሃገራቱ ግንኙነታቸውን ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት ለማሳደግም ስምምነት ደርሰዋል።

በተጨማሪም ፕሬዚዳንት አል ሲ ሲ በሊቢያ የባህር ዳርቻዎች በአሸባሪው አይ ኤስ የተገደሉ ኢትዮጵያውያን አስከሬንን ለማግኘት በሚደረገው ጥረት ሃገራቸው እገዛ እንደምታደግርም ቃል ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በዑጋንዳ ለሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ከዚያ በፊትም በጂቡቲ፣ በሱዳን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና የተባበበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ጉብኝት ማድረጋቸውም የሚታወስ ነው።