ኢትየጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሰሞኑን ያደረጉት ዉይይት ዉጤታማ እንደነበር የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት09 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የሶስቱ ሀገራት የዉጭ ጉዳይ፣ ዉሃ ሀብት ሚኒስትሮችና የደህንት ሃላፊዎች ያካሄዱት ስብሰባ ሀገራቱን ይበልጥ ያቀራረበ መሆኑን ተናግረዋል።

ውይይቱ ሁሉም ሀገራት የተግባቡበትና የራሳቸዉን ጥቅም ያስከበሩበት መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ በተለይም ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን ያስጠበቀችበት ነው ብለዋል።

 

ተሳታፊዎቹ በግድቡ ዉሃ ሙሌትና አለቃቅ ላይ ጥናት የሚያከናዉኑ የተመራማሪዎች ቡድን እንዲዋቀር ስምምነት ላይ ደርሰዋል ብለዋል።

 

እነዚህ አጥኝ ቡድኖችም በ3 ወራት ዉስጥ ስራቸዉን የሚያጠናቅቁ ሲሆን፥ የደረሱበትን ዉጤትም ለዉሃ ሀብት ሚኒስተሮቹ የሚያቀርቡ ይሆናል ተብሏል።

 

ውይይቱ ከዚህ ቀደም ከተደረጉት መሰል ስብሰባዎች የተሻለ ዉጤት የተገኘበት መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

 

ሶስቱ ሀገራት የመሰረተ ልማት ኢንቨስተመንት ፈንድን ለማቋቋም ስምምነት ላይ ደርሰዋል ተብሏል።

ሀገራቱ ፋይናንስና የፈንዱ ማቋቋሚያ ሰነዶች ከወዲሁ የሚዘጋጁ ሲሆን፤ በቀጣዩ ግንቦት 26 እና 27 ሚኒስተሮች ካይሮ ተገናኝተዉ ዉይይት በማድረግ ስምምነቱ የሚፀድቁ ይሆናል ተብሏል።

 

እነዚህን ስራዎች ለመግምገመም በመሪዎች ደረጃ በ የ6 ወራቱ በየሀገራቱ በዙር ዉይይት እንደሚደረግም ነው ዶ/ር ኢንጂነር ስለሽ የገለጹት።

 

በዚህም በግድቡ የዉሃ አሞላል፣ አለቃቅ፣ በአካባቢና በማህበረሰቡ ላይ የሚያሳድረዉን ተፀእኖ ራስን በቻለ ሳይንሳዊ ጥናት ለማካሄድ ከሶስቱ ሀገሮች የተወጣጡና ከእያንዳንዳቸዉ አምስት አባላት ያሉት ቡደን ለማቋቋም ስምነነት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

አጠቃላይ ዉይይቱ በህዳሴ ግደቡ ላይ ለነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ያደረገ ነዉ ያሉት ዶክተር ኢንጅነር ስለሽ በቀለ ለቀጣይ ስራዎችም አጋዥ ተደርጎ የሚወሰድ ነው ብለዋል።

በቀጣይም በሶስቱ ሀገራት መካከል የታላቁ የኢትየጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በመሰረተ ልማቶች ላይ ተባብሮ ለመስራት መሰል ዉይይቶች የሚቀጥሉ መሆኑንም ተናግረዋል።

 

በተመስገን እንዳለ