የግንቦት 20 የድል በዓል ሲከበር የለውጥ እንቅስቃሴውን ከዳር በማድረስና ተጨማሪ ድሎች ለማስገንዘብ ህዝቡ ሊረባረብ ይገባል- መንግስት

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዘንድሮውን የግንቦት 20 ድል በዓል ስናከብር የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ከዳር በማድረስ ተጨማሪ ድሎች ለማስገንዘብ መላው ህዝብ እንደወትሮው ሊረባረብ እንደሚገባ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት አስታወቀ።

የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚንስትር አቶ አህመድ ሽዴ ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው የግንቦት 20 ድል በዓልን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ አህመድ በመግለጫቸውም፥ የዘንድሮው የግንቦት 20 ድል በዓል "የላቀ ብሄራዊ መግባባትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለላቀ አገራዊ ስኬት" በሚል መሪ ቃል ይከበራል ብለዋል።

በዓሉም በመላ ሀገሪቱ እንዲሁም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሚገኙባቸው የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ሚሲዮኖች በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበርም አስታውቀዋል።

አቶ አህመድ ሽዴ እንዳሉት፥ የግንቦት 20 ድል የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብዝሃነትን ያከበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ በከፈሉት መስዋእትነት የተገኘ ውጤት ነው።

ይህ ቀን አዲሲቷ ኢትዮጵያ እንድትገነባ መሰረት የጣለና የሀገሪቱ ዜጎች ማንነታቸው ተከብሮ በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለመገንባት የሚያስችል ህገ-መንግስታዊ ዋስትና ያገኙበት እለት ነውም ብለዋል አቶ አህመድ።

የግንቦት 20 ድል በዓል የሀገሪቱ የወደፊት ተስፋ እንደገና እንዲያንሰራራ በማድረግ እንደ አገር ለመቀጠል ተደቅኖ የነበረውን ስጋትና ሁኔታ የቀየረ መሆኑንም ገልፀዋል።

ሁሉንም ህዝቦች የሚያስተባብር አዲስ የፖለቲካ ስርዓት በመገንባት የሀገሪቱን ህልውና ያስቀጠለ መሆኑንም ሀላፊ ሚኒስትሩ አውስተዋል።

የግንቦት 20 ድል የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ፣ ፈጣን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ለማረጋገጥ መሰረትና ዋስትና መሆን የቻለ መሆኑንም አቶ አህመድ አንስተዋል።

ይህም የሆነው በሀገሪቱ ውስጥ ብዝሃነት የተቀበለና ያከበረ አዲስ ህገ መንግስታዊ ስርዓት መፍጠር ስለተቻለ መሆኑም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ሂደት ውስጥ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች መንግስት በጥሞና በመመልከት ችግሮቹ በዘላቂነት የሚፈቱበትን መሰረታዊ መፍትሄዎች ማስቀመጡንና የመፍትሄ እርምጃዎችንም መውሰድ መጀመሩንም ሃላፊ ሚንስትሩ ገልፀዋል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች የዘንድሮውን ግንቦት 20 በሚከበርበት ወቅት የወደፊቱን ተስፋ እውን የሚደረግበት እንደመሆኑ በሀገር ግንባታ ሂደት የሁሉም ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ከመንግስት ጎን እንዲቆም ነው ፅህፈት ቤቱ ጥሪ ያቀረበው።