ሁለተኛው የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ማሳለጫ ስብሰባ በአዲስ አበባ ተጀመረ

አዲስ አባበ፣ ግንቦት 09፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሁለተኛው የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ማሳለጫ ስብሰባ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።

የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኢጋድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀመንበር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ስብሰባው ሲጀመር ባደረጉት ንግግር፥ የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች በመሀላቸው ያለውን የጥርጣሬ መንፈስ በማስወገድ የተኩስ ስምምነት እንዲያከብሩና እንዲያቆሙ እና ልዩነታቸውን እንዲያጠቡ ጠይቀዋል።

የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አቶ ሀይለማሪም ደሳለኝ ለደቡብ ሱዳን ሠላም ስኬት ሁለንታናዊ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበሩ ያስታወሱት ዶ/ር ወርቅነህ፥ ለደቡብ ሱዳን የሠላም ስምምነት ትግበራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይም ትኩረት የሚሰጡት ጉዳይ መሆኑንም ገልፀዋል።

ለደቡብ ሱዳን መረጋገት ዋና ተዋናዮች የአገሪቱ ፖሊቲካኞች እንደሆኑ ሌሎች ወገኖች የደጋፊነት ሚና ብቻ እንደላቸው ተናግረዋል።

ለተሳታፊዎቹ ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ስብሰባው ፍሬ እንዲያፈራ ተሳታፊውን አሳስበዋል።