የኮንትሮባንድ ንግድ ሲያከናውኑ የነበሩ 13 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 8 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በተደራጀ መልኩ የኮንትሮባንድ ንግድ ሲያከናውኑ የነበሩ 13 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ገለፁ።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፥ መንግስት በተደራጀ መንገድ የኮንትሮባንድ ስራዎች የሚያከናውኑ ግለሰቦችንና የትስስር መረቡን ተከትሎ በቁጥጥር ስር የማዋል ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።

በዚህም ከሰሞኑ በህገ ወጥ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉንም ነው የተናገሩት።

በዋናነትም የኮንትሮባንድ ንግዱ በተደራጀ መንገድ በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ቅድሚያ በመስጠት ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ ተሰርቷልም ነው ያሉት።

በተለይም የገቢና ወጪ ንግዱ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ላይ የመጀመሪያ ዙር ተጠርጣሪ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር የማዋል ዘመቻ የሚከናውኑባቸው አካባቢዎች እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል።

ሃላፊ ሚኒስትሩ ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባና አካባቢው፣ ከአዋሽ እስከ ጋላፊ ባለው የልማት ኮሪደር መስመር፣ በዲላ ሞያሌ መስመር እንዲሁም በኦሮሚያና በአፋር የተለያዩ አካባቢዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

እንደ ሃላፊ ሚኒስትሩ ገለጻ ተሽከርካሪዎች፣ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች፣ አልባሳት እና ቆርቆሮዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በኮንትሮባንድ ድርጊት ላይ ከተሰማሩት በተጨማሪ ህጋዊ ፍቃድን ሽፋን በማድረግ በህገ ወጥ መንገድ ዜጎችን ወደተለያዩ የዓረብ ሃገራት ሲልክ የነበረ አንድ ተቋምን የማሸግና በግለሰቦች ላይም እርምጃ ተወስዷል።

መሰል እርምጃዎችም ተመሳሳይ ድርጊት በሚፈጽሙ ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት ሃላፊ ሚኒስትሩ።

መንግስት የዜጎችን መብትና ክብር እንዲጠበቅ ከሚያከናውነው ተግባር ባለፈም ቤተሰብ ልጆቹን ለስራ ስምሪት በህጋዊ መንገድ ብቻ መላክ እንዳለባትም አሳስበዋል።

ለዚህም መንግስት በየጊዜው ከተለያዩ ሃገራት ጋር ህጋዊ ስምሪት ለማድረግ ስምምነት የተደረገባቸው ሃገራት ዝርዝር ይፋ ማድረጉን እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

በኮንትሮባንድም ይሁን በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ዝርዝር በቀጣይ ይፋ እንደሚደረግም አንስተዋል።


በበላይ ተስፋዬ