በዛምቢያ ታስረው የነበሩ 20 ዜጎች ወደ ሀገራቸው ሊመለሱ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዛምቢያ እስር ቤቶች ውስጥ ታስረው የነበሩ 20 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ሊመለሱ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  አስታወቀ፡፡

በህገ-ወጥ መንገድ በአዘዋዋሪዎች አማካኝነት ድንበር አቋርጠው ደቡብ አፍሪካ ለመግባት በመጓዝ ላይ ሳሉ በፖሊሶች ተይዘው በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች የቆዩ ናቸው ተብሏል፡፡ 

ዛምቢያን በሚሸፍነውና ዚምባቢዌ በሚገኘው የኢፌዴሪ ኤምባሲ እና በዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የጋራ ጥረት ነው ወደ ሀገራቸው የሚመለሱት።

ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች ከ20 እስከ 30 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው ተብሏል።

ባለፈው መጋቢት ወር ውስጥ በዛምቢያ በእስር ላይ የቆዩ 47 ኢትዮጵያዊያን መንግስት ባደረገው ጥረት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ይታወሳል።

ባሳለፍነው ሳምንትም 1400 ኢትዮጵያዊያን በሱዳን ከእስር ተለቀው ከቤተሰቦቻቸው ጋር የተቀላቀሉ መሆናቸው አይዘነጋም። 

በተመሳሳይ በኬንያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እስረኞችን ለማስፈታት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  አስታውቋል።