የአውሮፓ ህብረት የኢራን የኒውክሌር ስምምነት ለመታደግ ዘጠኝ የኢኮኖሚክ ዕቅዶችን አወጣ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፈረንሳይ፣ ጀርመንና ብሪታንያ የኢራን የኒውክሌር ስምምነትን ለመታደግ ዘጠኝ የኢኮኖሚክ ዕቅዶችን መንደፋቸውን አስታወቁ፡፡

ይህንን ያሉት ቤልጄይም ብራሰልስ ላይ በተካሄደው ከኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡

ዕቅዶቹ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ፥ ከነዚህም መካከል ከኢራን ጋር ያለውን የኢኮኖሚ ግንኙነት ማስቀጠል፣ ኢራን ነዳጅና ጋዝ የመሸጥ ቀጣይነት ላይና በኢራን የሚገኙ የአውሮፓ ካምፓኒዎችን ከለላ መስጠት ላይ ያተኮሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄኮ ማስ አሜሪካን ከስምምነቱ ራሷን ማግለሏን ተከትሎ የተፈጠረውን ሁኔታ ማርገብ ቀላል አይደለም ብለዋል፡፡

እንዲሁም የብሪታንያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በስምምነቱ መቆየት ለጋራ ሰላማችን ትልቅ ቦታ ስላለው ተፈጻሚ እንዲሆን ከአጋሮቻችን ጋር እንሰራለን ብለዋል፡፡

የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሃመድ ጃቫድ ዛሪፍ ትብብሩ መልካም ጅምር ላይ መሆኑን አንስተው፥ ሂደቱ ገና መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ሶስቱ የአውሮፓ ሀገራት ከኢራን ጋር በባለሙያዎች ደረጃ በቀጣይ ሳምንት በቬይና ተገናኝተው ለመወያየት ቀጠሮ መያዛቸውን የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገልጸዋል፡፡

 


ምንጭ፦አልጀዚራ
በአብርሃም ፈቀደ ወደ አማርኛ ተመለሰ