ጓቴማላ በእስራኤል የሚገኘው ኤምባሲዋን ወደ እየሩሳሌም አዛወረች

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 8 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ጓቴማላ በእስራኤል የሚገኘው ኤምባሲዋን ከቴል አቪቭ ወደ እየሩሳሌም በይፋ አዛወረች።

ኤምባሲውን የማዛወር ስነ ስርዓቱ የጓቴማላው ፕሬዚዳንት ጂሚ ሞራሌስ እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በተገኙበት በዛሬው እለት ተከናውኗል።

ጓቴማላ ከአሜሪካ ቀጥሎ ኤምባሲዋን ወደ እየሩሳሌም ያዛወረች ሁለተኛዋ ሃገር ሆናለች።

ከትናንት በስቲያ ሰኞ አሜሪካ ኤምባሲዋን ከቴል አቪቭ ወደ እየሩሳሌም በይፋ ማዛወሯ የሚታወስ ነው።

የአሜሪካን ውሳኔ ፈረንሳይና የዓረብ ሊግ ህገ ወጥ በማለት ኮንነውታል።

አሜሪካ ኤምባሲዋን ወደ እየሩሳሌም ማዛወሯን ተከትሎ የእስራኤል ጦር፥ በጋዛ ሰርጥ ለተቃውሞ በወጡ ፍልስጤማውያን ላይ በወሰደው እርምጃ ከ60 በላይ ፍልስጤማውያን ለህልፈት ተዳርገዋል።

ይህን ተከትሎም የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በትናንትናው እለት አስቸኳይ ስብሰባ አድርጓል።

በስብሰባው ወቅት ኩዌት ሃገራት ኤምባሲያቸውን ከቴል አቪቭ ወደ እየሩሳሌም እንዳያዛውሩ እና ከፍልስጤማውያን ግድያ ጋር በተያያዘ ጉዳዩን የሚያጣራ ገለልተኛ አካል እንዲቋቋም የሚጠይቅ ረቂቅ ሃሳብ አቅርባለች።

አሜሪካ በበኩሏ የኩዌትን ረቂቅ ውድቅ አድርጋዋለች።

ከፈረንጆቹ 1967 ጀምሮ ምስራቃዊ እየሩሳሌም በእስራኤል ቁጥጥር ስር ትገኛለች።

ከዚያን ጊዜ ወዲህም እስራኤል ሉዓላዊ ግዛቷ እንደሆነች ስትገልጽ ቆይታለች።

ፍልስጤማውያን በበኩላቸው እየሩሳሌም የወደፊቷ ዋና ከተማቸው እንደሆነች ይገልጻሉ።


ምንጭ፦ አልጀዚራ