ባለሃብቶች እና ማህበራት ብድር ወስደው በደን ልማት ላይ እንዲሰማሩ የሚያግዝ የደን ፈንድ ሊቋቋም ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ የግል ባለሃብቶች እና ማህበራት ብድር ወስደው በደን ልማት ላይ እንዲሰማሩ የሚያግዝ የደን ፈንድ ለማቋቋም የሚያስችል ረቂቅ አዋጅም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከዚህ ቀደም የግልና የማህበራት ደን አልሚዎች ተሳትፎ አናሳ መሆንና የባንኮች የብድር ስርአት ለደን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ምቹ አለመሆኑ ፈንዱን ለማቋቋም ምክንያት እንደሆነ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።።

ኢትዮጵያ ከ50 በመቶ በላይ መሬቷ ተራራማ በመሆኑ ለደን ልማት ምቹ እንደሆነ ይነገራል።

ከሀገሪቱ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት እየታረሰ ያለው መሬት 20 በመቶው ብቻ የሚሸፍን ሲሆን፥ የሀገሪቱ ከ80 በመቶ በላይ ህዝብ ህይወቱ የተመሰረተው ከሀገሪቱ ስፋት አንድ አምስተኛው መሬት ላይ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ከ50 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ መሬት ለደን ልማት ምቹ ቢሆንም ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያላቸው ድርሻ ከ6 በመቶ እንማይበልጥ ነው የተነገረው።

በአንፃሩ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የሀገሪቱን የቆዳ ስፋት 20 በመቶ ቢሸፍንም ቀዳሚው የኢኮኖሚ ዋልታ እንደሆነ ይታወቀል።

የአካባቢ፣ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴርም ደኖችን በመጠበቅ ከሚገኘው ዘርፈ ብዙ ጥቅም ባሻገር በዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ትኩረት እየተሰራ መሆኑ ይነገራል ።

ለስርአተ ምህዳር ጥበቃ ከሚያስፈልጉት ውጭ ሰው ሰራሽ ደኖችን አልምቶ ለገበያ በማቅረብ በርካቶች ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውንም ታውቋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ከበደ ይማም እንደተናገሩት ባለፈው አመት ከዘርፉ የወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ ለዚህ ማሳያነት
ጠቅሰዋል።

የአማራ ክልል የአካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ በበኩላቸው ከደን ልማት የሚገኘው ገቢ ከሰብል እርሻው የተሻለ ውጤት እያሰገኘ በመሆኑ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የእርሻ መሬቶች ወደ ደን ማልሚያነት እየተለወጡ መምጣቸውን ገልፀዋል።

ሆኖም እንደ ሀገር በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች እና ማህበራት በቁጥር ዝቅተኛ እንደሆኑ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት።

በአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር የፖሊሲ ባለሙያ አቶ ብርሃነ በዛብህ በዚህ አመት የወጣው የደን አዋጅ ደንን የግል፣ የማህበረሰብ፣ የማህበራት እና የመንግስት በማለት መክፈሉን ተናግረዋል።

ባለሃብቶች ከባንክ ለደን ልማት ብድር የሚወስዱበት የወለድ መጠን ከ9 እስከ 14 በመቶ በመሆኑ ደኖችን በግልም ሆነ በማህበራት ለማልማት ከባድ ያደርገዋል ብለዋል።

ደን ለምቶ ጥቅም ላይ እስኪውል ከ15 እስከ 50 አመት የሚወስድ በመሆኑ የወለድ መጠኑ ክፍ እንዲል ስለሚያደርገው የግል አልሚዎች ዘርፉን ምርጫቸው እንደማያደርጉትም ብለዋል።

የብድር ቆይታ ጊዜውም ከ15 አመት እስከ 20 አመት ብቻ የሚቆይ መሆኑ ሌላኛው ባለሀብቶች በዘርፉ እንዳይሰማሩ የሚያደርግ ተግዳርት እንደሆነ ባለሙያው አንስተዋል።

በዚህም መሰረት በዘርፉ ለሚሰማሩ አካላት ልዩ ብድር ማቅረብ የሚያስችል አሰራር መዘርጋት የሚያስችል የደን ፈንድ ለማቋቋም እየተሰራ ነው ብለዋል።

የደን ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጅም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተልኳል ነው ያሉት።

ይህን ፈንድ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል የገንዘብ ምንጭም እንዳለ ባለሙያ አስታውቀዋል።

ከዚህ ውስጥ ደኖች የካርበን ልቀትን በመቀነስ ወሳኝ በመሆናቸው ኢትዮጵያ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ የምታገኘው ገቢ አለ ተብሏል።

በደን ልማት ላይ የሚሰማሩ ባለሃብቶችም ሆኑ ማህበራት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቅ ካርበንን በመቀነስ ከሚያገኙት ገቢ ላይ ግብር ተጥሎ የደን ፈንዱ ከዚህ ድርሻ እንዲኖረው ይደረጋል።

አዋጁ ከፀደቀ በኋላ በሚወጣው ደንብ መሰረት በካርበን ልቀት ላይ የሚጣለው ግብር መጠን በቀጣይ እንደሚወሰንም ተነግሯል።

ሌላኛው የፈንዱ የገንዘብ ምንጭ ከደን ስርአተ ምህዳር አገልግሎት የሚጣል ግብር ነው።

ከምንተነፍሰው ንፁህ አየር ጀምሮ እስከ ሚጠጣ የምንጭ ውሃ የደኖች ሚና ወሳኝ በመሆኑ በጫካ ቡና፣ በታሸጉ የውሃ ምርቶች እና በፓርኮች ላይ ግብር በመጣል ለደን ፈንዱ ገቢ ይደረጋል ተብሏል።

ረቂቅ የደን ፈንድ አዋጁ በመንግስት ብቻ ሲለማ የነበረውን ደን ማህበራት እና የግል ባለሃብቶች እንዲሰማሩበት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።

ይህም ደኖች ለኢኮኖሚው ያላቸው አበርክቶ እንዲያድግ ያግዛል ነው የተባለው።

ረቂቅ አዋጁ ከደን ፈንዱ ብድር የሚወስዱ አልሚዎች እስከ 35 አመት የሚደርስ የገንዘብ ብድር እንዲያገኙ ያስችላል፤ ወለዱም በብሄራዊ ባንክ የሚወሰን ቢሆንም እጅግ አነስተኛ እንደሚሆን ተገልጿል።

አልሚዎች የወሰዱትን ብድር ተጠቅመው ያለሙትን ደን ቆርጠው ከሸጡ በኋላ ብድራቸውን ሲመልሱም ብድሩ ለሌሎች አልሚዎች እንደሚተላለፍ ተነግሯል።


በፋሲካው ታደሰ