የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ውይይት በአዲስ አበባ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የኢትዮጵያ ፣የሱዳን እና የግብፅ ከፍተኛ የሚኒስትሮች የሚሳተፉበት የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ስብሰባ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ሁለተኛው የኢትዮጵያ ፣ የሱዳን እና የግብፅ ከፍተኛ የሚኒስትሮች በስኬት መጠናቀቁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በስብሰባውም ሶስቱ አገሮች የሶስትዮሽ መሠረተ ልማት ፈንድ ለማቋቋም፣ የህዳሴ ግድብ አሞላል የሚያጠና ብሔራዊ ገለልተኛ የአጥኝዎች ብድን ለማቋቋም እና ለአማካሪ ድርጅቱ ጥያቄዎች እና አስተያየትን ለማቅረብ ተስማምተዋል።

በስብሰባው ላይ የሶስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ፣ የውሃ ሃብት ሚኒስትሮች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሌሎች ኃላፊዎች በውይይቱ ተሳታትፈዋል።

በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ኢትዮጵያ የሶስትዮሽ ውይይቱ ውጤታማ እንዲሆን በሙሉ ልብ እንደምትሰራ አስታውቀዋል።

ሁለተኛው ስብሰባ የተካሄደው የሶስቱ አገራት መሪዎች ባለፈው ጥር ወር ባደረጉት ስብሰባ ሚኒስትሮቻቸው በጋራ መስራት እንዲችሉ ያስተላለፉትን መመሪያ መሠረት በማድረግ እንደሆነ ተገልጿል።

ከሳምንት በፊት የሶስቱ ሃገራት የውሃ ሃብት ሚኒስትሮች 18ኛ ስብሰባቸውን በአዲስ አበባ ማካሄዳቸው ይታወሳል።

በስብሰባው የሃገራቱን የጋራ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ ምክክሮችን አድርገዋል።

በውይይታቸው ወቅትም ባላለቁ ሪፖርቶች ላይ ምክክር ማድረጋቸው መገለጹ ይታወሳል።

ሶስቱም ሀገራት ከወር በፊት በሱዳን ካርቱም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።

በውይይታቸውም የመሰረተ ልማት ፈንድ በማቋቋም፣ በኢንቨስትመንት እና ሌሎች መስኮች ላይ በመስራት የሀገራቱን የንግድ ትስስር ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው የሚታወስ ነው።