አዲሱ የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር የስልጣን ቆይታቸው ከ2 ዓመት እንደማያልፍ ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቅርቡ የተመረጡት አዲሱ የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ማሃቲር ሞሀመድ በስልጣን ላይ ለአንድ ወይም ሁለት ዓመት ብቻ እንደሚቆዩ ገለፁ።

የ92 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር መሃቲር በምትካቸውም በአሁኑ ወቀት በእስር ላይ የሚገኙት አንዋር ኢብራሂም ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆኑ እንደሚችሉ አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙትና በተራማጅ አስተሳሰባቸው የሚታወቁት አንዋር ኢብራሂም በነገው እለት ከእስር እንደሚፈቱም ተነግሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር መሃቲር አክለውም የሀገሪቱ መንግስት በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ራዛክ ላይ በቅርቡ የሙስና ክስ ሊመሰርት እንደሚችልም ገልፀዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ማህቲር እና እስር ላይ በሚገኙት አንዋር የሚመራው የአራት ፓርቲዎች ጥምረት ባሳለፍነው ሳምንት በሀገሪቱ የተካሄደውን ምርጫ ማሸነፋቸው ይታወሳል።

ማሃቲርም ባሳለፍነው ሳምንት ሀሙስ ላይ የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ቃለ መሃላ መፈፀማቸው ይታወሳል።

ምንጭ፦ www.reuters.com