የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት በታቀደለት ጊዜ ባለመጀመሩ ህገ ወጥ ጉዞን አማራጭ ማድረጋቸውን አስተያየት ሰጭዎች ተናገሩ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 6 ፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት በታቀደለት ጊዜ ወደ ተግባር ባለመግባቱ ህገ ወጥ ጉዞን እንዲመርጡ እንዳደረጋቸው አስተያየት ሰጭዎች ተናገሩ።

አስተያየት ሰጭዎቹ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት፥ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪቱ በታቀደለት ጊዜ ወደ ስራ ባለመግባቱ ሳቢያ ህገ ወጥ ጉዞን አማራጭ ማድረግ ጀምረዋል።

ወደ ዱባይ እና ሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ለ15 ቀን የንግድ ቪዛን በመጠቀም እስከ 20 ሺህ ብር ከፍለው እንደሚጓዙም ነው የተናገሩት።

በጅማ ዞን ጥራ ፈታ ወረዳ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ስራ ሂደት ሃላፊ የሆኑት ወይዘሮ ታጉ ጌታቸው፥ ደላሎቹ ገጠር አካባቢዎችን መርጠው በሚያደርጉት የማማለያ ዘዴ ሳቢያ ግለሰቦቹ ይህን መንገድ እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።

ይህን መሰሉን ችግር መቅረፍ የሚያስችለው የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት አዋጅ ቢፀደቅም ወደ ስራ ለማስገባት ግን በርካታ ጊዜን ወስዷል።

መንግስት በያዝነው አመት ጥር ወር ላይ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት እገዳውን ማንሳቱን ይፋ ማድረጉን ተከትሎም፥ ሰዎች የውጭ ሀገር የስራ ስምሪቱ ወደ ስራ ገብቷል በሚል በንግድ እና በሃገር ጎብኝ ቪዛ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ያመራሉ።

መንግስት ከኳታር እና ዮርዳኖስ ጋር የተፈራረማቸው የስራ ስምምነቶች መጽደቃቸውን የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሳምንት በፊት መግለጹ ይታወሳል።

ከዚህ ባለፈም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከኩዌት ጋር የስራ ስምሪት ማድረጉን መግለጹም የሚታወስ ነው።

ነገር ግን ስምምነቱ 5 አመት የሞላው እና ሀገሪቱ ካወጣችው አዲስ የሰራተኞች ህግ ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ስምምነቱ እስከሚሻሻል ድረስ እንዲዘገይ መደረጉን፥ በሚኒስቴሩ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አበራ አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር የተደረሰውን ስምምነት ወደ ስራ ለማስገባት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የሚፀድቅበት ቀን እየተጠበቀ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ በበኩላቸው፥ የሳዑዲ ዓረቢያን ስምምነት የተመለከተ ምንም አይነት ረቂቅ አዋጅ ለምክር ቤቱ አልቀረበም ብለዋል።

ሰብሳቢዋ የምክር ቤቱ የአባላት እና ደንብ የአሰራር ስነ ምግባር የመጀመሪያ ንባብ ተደርጎ ለቋሚ ኮሚቴው ከተመራ አዋጅን ለማፅደቅ ከሀያ ቀን በላይ አይቆይምም ነው የሚሉት።

ምክር ቤቱ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያዎች መስጠቱን ያነሱት ሰብሳቢዋ፥ በምክር ቤቱ የስድስት ወራት ግምገማም የውጭ ሀገር የስራ ስምሪቱ ከሚገባው በላይ እንደዘገየ መገምገሙን ጠቅሰዋል።

የዘጠኝ ወር ግምገማ ሲደረግም ለውጥ ከሌለ የሚመለከተው አካል የእርምት እርምጃ እንዲወስድ እንደሚደረግ አንስተዋል።

አሁን ላይ ከ58 በላይ ኤጀንሲዎች የብቃት ማረጋጋጫ እንደተሰጣቸው ከሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ማንኛውም ዜጋ የውጭ ሀገር ስምሪትን ለማስፈፀም የወጣውን አዋጅ እና የሚጠይቀውን መስፈርት በማሟላት፥ በሚስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ ውላቸው ፀድቆ እና ልዩ መታወቂያ ሲሰጣቸው ብቻ ጉዞ ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራል።

ከዚህ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም ጉዞ ግን ህገወጥ መሆኑንም ገልጿል።

ይሁን እንጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መስራት ያለበትን ስራ ባለመስራቱ አሁንም ድረስ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በህጋዊ ሽፋን ወደ መካከለኛው ምስራቅ መጓዛቸውን ቀጥለዋል።

በተመስገን እንዳለ