ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የኤች.አይ.ቪን ስርጭት መቆጣጠር የሚያስችል አሰራር እየተከተሉ አይደለም ተባለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አብዛኛዎቹ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የኤች አይ ቪ/ኤድስን ስርጭት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችል የተደራጀ አሰራር እንደማይከተሉ የፌደራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት ይገልጻል።

እድሜያቸው ከ15 እስከ 24 የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ለኤች አይ ቪ/ኤድስ ቫይረስ ተጠቂ መሆናቸውን፥ ከፌደራል ኤች አይ ቪ (ኤድስ) መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የፅህፈት ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ገብረመድህን ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የኤች አይ ቪ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የተሰራው ስራ አጥጋቢ አይደለም ይላሉ።

ለዚህም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያሉ አመራሮች ለፀረ-ኤድስ ፕሮግራም ትኩረት ባለመስጠታቸው ሳቢያ በቂ ስራ አለመሰራቱ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

የተወሰኑ የትምህርት ተቋማት የተሻለ እቅድ አውጥተው የሚሰሩ እንዳሉ ሳይዘነጉ አብዛኛዎቹ ግን የዚህ ሰለባ ናቸው ብለዋል።

የደቡብ ክልል ቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት እና ስልጠና ቢሮ የኤች አይ ቪ (ኤድስ) ጉዳዮች አስተባባሪ አቶ ዞሪ ባልቻ ደግሞ፥ በፀረ-ኤድስ ዙሪያ በትምህርት ተቋማት ተሰሩ ተብለው የሚቀርቡ የስራ አፈፃፀም ሪፖርቶችም በጥንቃቄ ሊፈተሹ ይገባል ነው የሚሉት።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በስፋት እና በጥልቀት መስራት ላይ ክፍተት ስለመኖሩ በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ዘርፍ ኤች አይ ቪ እና (ኤድስ) ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሙሴ ተስፋው ይናገራሉ።

አቶ ሙሴ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ አደንዛዥ ዕጾች መበራከታቸው ለኤች አይ ቪ ስርጭት መስፋፋት ምክንያት መሆኑንም ነው የሚናገሩት።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ትምህርት ሚኒስቴር እነዚህን ነገሮች ለማስቆም የተጓዘበት መንገድ እምብዛም የሚባልና ብዙ የሚቀረው መሆኑ ይነገራል።

ከዚህ ባለፈም መንግስት ለፀረ ኤች አይ ቪ ኤድስ ፕሮግራም የሰጠውን ትኩረት ያህል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች አለመስጠታቸውም ለችግሩ በምክንያትነት ይጠቀሳል።

ይሁን እንጅ በዩኒቨርሲቲዎች እና በትምህርት ተቋማት አካባቢ እነዚህን አዋኪ ነገሮች ማስቆም የሚረዳ ህግ በመዘጋጀት ሂደት ላይ መሆኑን አቶ ሙሴ ይገልጻሉ።

ለፀረ ኤች አይ ቪ እና ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ፕሮግራም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ካልሰጡት መዘዙ ከባድ ነው መሆኑን ያነሱት ደግሞ፥ የፌደራል ኤች አይ ቪ (ኤድስ) መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ገብረመድህን ናቸው።

ኤች አይ ቪ በምጣኔ ሀብት ላይ ከፍ ያለ ጫና እንደሚያደርስ የጠቀሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፥ ባለፉት ሶስት አመታት ብቻ ለፀረ ኤች አይ ቪ እና ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ፕሮግራም 7 ቢሊየን ብር ወጪ መደረጉን ጠቁመዋል።

በቀጣይም ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ዘርፉ የፀረ-ኤድስ እንቅስቃሴን ለማጠናከር ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራሁ ነው ብሏል።


በስላባት ማናዬ