የኦሮሚያ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ አዚዛ አብዲ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ክልል ሴቶች እና ህፃናት ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ወይዘሮ አዚዛ አብዲ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተለያየ የሀላፊነት ቦታዎች ላይ ሲያገለግሉ የነበሩት ወይዘሮ አዚዛ ባደረባቸው የልብ ህመም ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት።

ወይዘሮ አዚዛ ከመስከረም 2008 ዓ.ም ጀምሮ የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ እንዲሁም ከጥቅምት 2009 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የኦሮሚያ ክልል የሴቶች እና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ በመሆን በማገልገል ላይ ነበሩ።

ከጳጉሜን ወር 2009 ዓ.ም አንስቶ እስካሁን ድረስ ደግሞ ካሉበት የሴቶች እና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ሀላፊነት በመተጨማሪም የኦህዴድ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል በመሆንም አገልግለዋል።

ወይዘሮ አዚዛ አብዲ ባጋጠማቸውን የልብ ህመም ሳቢያ ለህክምና ባመሩበት ህንድ ሀገር እያሉ ትናንት ምሽት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትም ለወይዘሮ አዚዛ አብዲ ቤተሰቦች እና ወዳጆች መፅናናትን ይመኛል።