ለ30 ሺህ የዓይን ህሙማን ነጻ ህክምና ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሳዑዲው አልባሳር ዓለም አቀፍ ግብረ ሠናይ ድርጅት ለ30 ሺህ ኢትዮጵያውያን የዓይን ህሙማን ነጻ ህክምና እንደሚሰጥ አስታወቀ።

አገልግሎቱ ከሚያዚያ 18 ቀን እስከ ግንቦት 7 ቀን 2010 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን በትግራይ፣ አፋርና ቤኒሻንጉል ጉምዝ የሚገኙ ህሙማንን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።

በድርጅቱ የኢትዮጵያ ተጠሪ መምህር ያሲን ራጁዑ፥ የአልባሳር ግብረ ሠናይ ድርጅት ዓይነ ስውርነትን ለመከላከል በኢትዮጵያ መንቀሳቀስ ከጀመረ አስር ዓመታት ማስቆጠሩን ተናግረዋል።

የዓይን ሕክምና አገልግሎቱን የሚሰጡ ከፓኪስታን የሚመጡ ዕውቅ ባለሙያዎች ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉም ነው ያሉት።

አገልግሎቱ በትግራይ ከሚያዚያ 18 እስከ ሚያዚያ 23 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ፥ በማይጨው ለምለም ካርል ሆስፒታል፣ በአፋር ከሚያዚያ 25 ቀን እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በዱብቲ ሆስፒታል፣ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ከግንቦት 2 እስከ 7 ቀን 2010 ዓ.ም በአሶሳ ሆስፒታል ይሰጣል ብለዋል።

ሕክምናው የዓይን ህሙማኑን መመርመር፣ መድሃኒት መስጠት፣ የመነጸርና ምክር አገልገሎትን እንደሚያካትት ጠቅሰው፥ ለአረጋውያንና የገንዘብ አቅም ለሌላቸው ታካሚዎች ቅድሚያ እንደሚሰጥ አመልክተዋል።

የአልባሳር ዓለም አቀፍ ግብረ ሠናይ ድርጅት በተለያዩ የእስያና አፍሪካ ሃገራት በመድሃኒት፣ በሆስፒታል ግንባታና በዓይን ሐኪሞች ማሰልጠኛ ኮሌጆች ግንባታ ይሳተፋል።

ኢትዮጵያ መንቀሳቀስ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶም እስካሁን ከ140 ሺህ እስከ 150 ሺህ ለሚደርሱ የዓይን ህሙማን የነጻ ሕክምና አገልግሎት መስጠቱን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።