የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በቻይና ጉብኘት ሊያደርጉ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሀንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በቻይና ይፋዊ የስራ ጉብኝት ሊያካሂዱ መሆኑ ተነግሯል።

የፊታችን አርብ ወደ ቻይና ያቀናሉ የተባሉት ሞዲ ከቻይናው ፕሬዚዳን ዢ ጂንፒንግ ጋር ተገናኝተው አንደሚወያዩ ተነግሯል።

የቻይና ከፍተኛ ዲፕሎማት የሆኑት ዋንግ ዪ እንደተናገሩት፥ ሁለቱ መሪዎች የፊታችን አርብ እና ቅዳሜ በማእከላዊ ቻይና ግዛት በምትገኘው ውሃን ከተማ ነው የሚገናኙት።

ከፍተኛ ዲፕሎማቱ ዋንግ ይህንን ያሉት ከህንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱሻማ ስዋራጅ ጋር ተገናኝተው ከተነጋገሩ በኋላ መሆኑም ታውቋል።

እንደ ዋንግ ገለፃ፥ በዢ ጂንፒንግ እና ናሬንድራ ሞዲ መሪነት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በአሁኑ ወቅት መልካም የሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል።

የሁለቱ መሪዎች ተገናኝቶ መወያየትም ሀገራቱ ወደፊት ግንኙነታቸውን የበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ያስችላቸዋል ብለዋል።

ምንጭ፦ www.reuters.com