በባህር ዳር ሲካሄድ የቆየው 7ኛው የጣና ፎረም ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 14፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በባህር ዳር ከተማ ለሁለት ቀናት የተካሄደው 7ኛው የጣና ፎረም ዛሬ ተጠናቋል።

በአፍሪካ ሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ የተወያየው የዘንድሮው 7ኛው የጣና ፎረም በትናንትናው እለት ነው በባህር ዳር መካሄድ የተጀመረው።

መድረኩ በዛሬው ዕለት የቀጠሎ ከተካሄደ በኋላ የተጠናቀቀ ሲሆን፥ ዛሬ በተካሄደው ውይይት አፍሪካ የራሷን ችግር በራሷ ለመፍታት መስራት ይኖርባታል ተብሏል፡፡

የቀድሞው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ባደረጉት ንግግር የአፍሪካ ሀገራት ግጭቶችን በራሳቸው መፍታት ይገባቸዋል፤ የሰላም ማስከበር ተልዕኮም ለረጅም ጊዜ መቀጠል የለበትም ብለዋል።

አያይዘውም የአፍሪካን ችግሮችን ውጫዊ ማድረግ የለብንም ሲሉም ተናግረዋል።

tana_g.jpg

የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴንጉን ኦባሳንጆ በበኩላቸው፥ ጊዜ የለንም፤ ችግሮችን እግር በግር ከወዲሁ እየፈታን መሄድ ይኖርብናል ብለዋል።

በተጨማሪም እንደ አንድ አገር ሳይሆን እንደአፍሪካ ተባብረን ለአፍሪካ ሰላምና ደህንነት መስራት ይኖርብናል ሲሉም ተናግረዋል።

ከውይይቱ በኋላም የጣና ፎረም አዲስ ሊቀ መንበር የተመረጠ ሲሆን፥ የቀድሞ የጋና ፕሬዚዳንት ጆን ድራህማኑ ማህማ አዲሱ የጣና ፎረም ሊቀ መንበር ሆነዋል።

አዲሱ የጣና ፎረም ሊቀ መንበር ጆን ድራህማኑ ማህማ የቀድሞው ከቀድሞው የጣና ፎረም ፕሬዚዳንትና ከሆኑት የቀድሞ የናጅሬሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጉን ኦባሳንጆ እጅ የሊቀመንበርነቱን ስፍራ ተቀብለዋል።

tana_n.jpg

በትናንትናው እለት የተጀመረው 7ኛው የጣና ፎረም በአፍሪካ ሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ነው ሲወያይ የነበረው።

ትናንት እለት መድረኩን በንግግር የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ተቋማዊ ማሻሻያዎችን በማድረግ አህጉሪቱ በራሷ ለመቆም እያደረገች ላለችው ጥረት ይህ መድረክ ጉልበት ይሆናል የሚል ተስፋም እንዳላቸው ነው የተናገሩት።

ይህም እድል ሊያመልጠን አይገባም ሲሉ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተናገሩት።