ስድስት የማዳበሪያ አይነቶች የአስገዳጅ ደረጃ ሊወጣላቸው ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ) ስድስት የማዳበሪያ አይነቶች አስገዳጅ ደረጃ እንደሚወጣላቸው ተነገረ።

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ከደረጃዎች ኤጀንሲ ጋር በመተባበር የአስገዳጅ ደረጃ መስፈርት ላይ ባለድርሻ አካላት ዛሬ አዋይተዋል።

በዚህ ወቅትም የኢትዮጵያ አፈር ሀብት ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ፋሲል ከበደ እንደተናገሩት ደረጃ የሚወጣላቸዉ ውህድ፣ ምጥን፣ ፈሳሽ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ፣ ቀጥተኛ እና ህያው የተባሉ የማዳበሪያ አይነቶች ናቸዉ።

ደረጃው ወደ ተግባር ሲገባ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚመረቱ ማዳበሪያዎች ጥቅም ላይ ከመዋላቸዉ በፊት በወጣዉ መስፈርት ፍተሻ እንዲደረግባቸው የሚያስገድድ ነው ተብሏል።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በቅድሚያ የአፈር ለምነትን እና ጤንነትን ማስጠበቅ እንደሚገባ ፕሮፌሰር ፋሲል ተናግረዋል ።

በቀረበዉ የጥናት ሰነድ ላይ ባለሙያዎች እና የዘርፉ ተመራማሪዎች የተካፈሉ ሲሆን አስገዳጅ ደረጃዉም በቀጣይ በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር በኩል ወደ ተግባር ይገባል ተብሏል።

በተመስገን አንዳለ