የሀገሪቱን ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የምሁራን ተሳትፎ የላቀ መሆን አለበት- ዶ/ር ደብረጽዮን

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሀገሪቱን ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የምሁራን ተሳትፎ የላቀ መሆን እንዳለበት የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለፁ።

የሶስት ቀናት ቆይታ የሚኖረው የትግራይ ክልል የምሁራን ኮንፍረንስ ዛሬ በመቐለ ከተማ ተጀምሯል።

ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እና ከውጭ ሀገራት የመጡ የትግራይ ክልል ተወላጅ ምሁራን በኮንፍረንሱ ላይ እየካፈሉ ነው።

3071_n.jpg

በኮንፍረንሱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፥ ከዚህ በፊት ህወሓትም ይሁን የክልሉ መንግስት ከምሁራን ጋር አብሮ ለመስራት የነበረው አካሄድ ችግር ነበረበት ብለዋል።

ይህም ህወሓት በጥልቀት ባካሄደው ግምገማ ተለይቷል ነው ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን።

በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት በሀገሪቱ የተፈጠረውን ችግር መነሻ በማድረግ የህዝቡን ችግሮች ለመፍታት ህወሓት እየገመገመ ነው ብለዋል።

ችግሮቹን ለመፍታትም ከምሁራን ጋር ቀድመን መገናኘት ነበረብን ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን፥ ከአሁን በኋላ ግን አብረን መስራት አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

ከችግር ለመውጣት በሚደረገው ጥረትም ምሁራን አጋዥ መሆን አለባቸው ሲሉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በቅርቡም ምሁራን በጥናትና ምርምር ለማገዝ ጥረት እያደረጉ መሆኑን እና ይህም ተስፋ ሰጪ እንቅስሴ መሆኑን ምክትል ርእሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም የነበሩ የህዝቡ ችግሮች በጥልቀት ተፈትሸው ተለይተዋል ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን፥ ምሁራኑ ደግሞ መፍትሄው ላይ ትኩረት አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባም ገልፀዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የመድረኩ ተሳታፊዎችም፥ ሀሳባቸውን በነፃ ለመግለጽ እና ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

መንግስትም የሚሰጡትን አስተያየቶች በፍጥነት ወደ ተግባር መቀየር መቻል አለበት ብለዋል።

በዛሬው እለት በመቐለ ተከማ መካሄድ የተጀመረው የትግራይ ክልል የምሁራን ኮንፍረንስ ለሶስት ቀናት ቀጥሎ የሚካሄድ ይሆናል።

በሙልጌታ አጽብሀ