በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተስተጓጉሎ የነበረው በረራ ወደ መደበኛ አገልግሎት ተመልሷል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ተስተጓጉሎ የነበረው የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በረራ ሙሉ በሙሉ ወደ መደበኛ አገልግሎት መመለሱ ተነገረ።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ በአሁኑ ወቅት የነበረው ችግር ተቀርፎ አውሮፕላኖች መንቀሳቀስ ጀምረዋል።

ዛሬ ጠዋት በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የአየር ተቆጣጣሪ ሰራተኞች ጋር ተፈጥሮ በነበረ አለመግባባት የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን በረራ ተስተጓግሎ እንደነበረ ይታወሳል።

በአሁኑ ሰዓት ግን የአየር ተቆጣጣሪ ሰራተኞች ጋር ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት በመቀረፉ ወደ መደበኛ ስራው መመለሱን እና አውሮፕላኖች ማረፍ እና መነሳት መጀመራቸውን ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው ተናግረዋል።