አሚሶም ከሶማሊያ ቀስ በቀስ የሚወጣበትን እቅድ አዘጋጀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2010 (ኤፍቢሲ) የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ በሶማሊያ (አሚሶም) ከሀገሪቱ ጦሩን ቀስ በቀስ የሚያስወጣበትን እቅድ አዘጋጀ።

የአሚሶም ከፍተኛ ኮማንደሮች በሞቃዲሾ ስብሰባ አካሂደዋል።

ከውይይት በኋላ የአፍሪካ ህብረት ባወጣው መግለጫ፥ የእቅዱ ትግብራ ውጤታማ እንዲሆን የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ እና የተገኙ ለውጦችን እንደሚያጠና አስታውቋል።

ይህ እቅድ ስኬታማ እንዲሆንም የሶማሊያ ብሄራዊ ጦር ያለውን የአቅም እና ሎጀስቲክ ብቃት የማጥናት እና አሚሶምም ይህንን እቅድ ለመተግበር የሚያስችለውን አቅም መታጠቁን የመመርመር ስራ እንደሚከናወንም ተመልክቷል።

አሚሶም በቆይታው ያገኛቸውን ስኬቶች ሀገሪቱን ለቆ ከወጣ በኋላም እንዲቀጥል አሁን ላይ ለተልዕኮው አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባም ነው የአሚሶም ዋና አዛዥ የተናገሩት።

በሌላ በኩል 1 ሺህ 822 የሚደርሱ የኡጋንዳ ወታደሮች በሶማሊያ የሚገኘውን የአሚሶም ጦር መቀላቀላቸው ተነግሯል።

በተጨማሪም ለስድስት ወራት ልምምድ ላይ መቆየታቸው የተገለጸ ሲሆን፥ በሶማሊያ የሚገኘውን የኡጋንዳ የሰላም አስከባሪ ኃይል ቁጥርን ከፍ አድርጎታል።

በ2017 የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በሶማሊያ ያለው የአሚሶም ጦር ቁጥር 21 ሺህ 626 እንዲሆን የወሰነ ሲሆን፥ የቆይታውንም ጊዜ እስከ 2018 ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ እንዲሆን ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

 

 


ምንጭ፦ ሲጂቲኤን
በአብርሃም ፈቀደ ወደ አማርኛ ተመለሰ