የግል ባለሃብቱ የኢኮኖሚው ዋስትና በመሆኑ መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 8 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የግል ባለሃብቱ የሃገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ዋስትና በመሆኑ በአሰራር እና በህግ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ መንግስት እንደሚሰራ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከግል ባለሃብቱ ጋር በሸራተን አዲስ በምግድና ኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኢንጅነር መላኩ አዘዘው በንግድና ኢንቨስትመንት ላይ በሚስተዋሉ ችግሮች ዙሪያ ያዘጋጁትን ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል።

በዚህም የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረትና የአጠቃቀም ችግር፣ የብድር አቅርቦት ችግር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እና የኢንቨስትመንት ዋስትና አለመኖር የዘርፉ ዋነኛ ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባለፈም ከሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ይልቅ ለውጭ ባለሃብቶች የሚሰጠው ድጋፍ ሌላው የዘርፉ ችግር መሆኑም ተጠቅሷል።

የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮችም በንግድ ዘርፍ እና ባጋጠሙ ችግሮች ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትና አጠቃቅም፣ የብድር አቅርቦት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር፣ ያልተገባ የንግድ ውድድር፣ በኢንቨስትመንቱ መስክ በሚታዩ ችግሮችና መሰል ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎች ቀርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ በዚህ የእድገት ደረጃ ላይ የሚገኝ ሃገር የሚያጋጥመው ችግር መሆኑን ጠቅሰው፥ እጥረቱን ለመቅረፍ ለውጭ ምንዛሪ ብክነት የሚዳርጉ አሰራሮችን ለማሻሻል እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ለዚህም ወደ ውጭ ሃገራት የሚደረጉ አላስፈላጊ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጉዞ ለዚህ ችግር እንደሚዳርግ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ችግሩን ለመቅረፍም በዚህ ረገድ ማሻሻያዎች ይደረጋሉም ነው ያሉት።

ከዚህ ባለፈም ከባለሃብቶች ለተነሳውና የውጭ ምንዛሪና ገንዘብን ወደ ተለያዩ ሃገራት በሚያሸሹ አካላት ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድም አስገንዝበዋል።

ከብድር ጋር በተያያዘም መንግስት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ዘርፎች በመለየትና ማሻሻያ በማድረግ ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለማሻሻል መንግስት ይሰራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዚህ ረገድ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍም ባለሃብቱ የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያና ምላሽ ባለሃብቱ ከባለሙያም ሆነ ከተቋም ማግኘት ያለበትንና መብቱ የሆነን አገልግሎት፥ በገንዘብ ከመግዛት በመቆጠብ የራሱን አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ጉቦን ባለመስጠትም መብቱ የሆነን አገልግሎት በመብቱ ሊያገኝ ይገባልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች የሃገሪቱ ኢኮኖሚና የብልፅግና ዋስትና ስለሆኑም መንግስት ለእነርሱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ ግን የውጭ ባለሃብቶችን ለውጭ ምንዛሪ፣ ለእውቀት ሽግግርና ቴክኖሎጅ እንዲሁም በአለም ገበያ ካላቸው ተፎካካሪነት አንጻር መንግስት እንደሚፈልጋቸውም ነው የተናገሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ መንግስት በተለይም ለግብርናው ዘርፍ የተለየ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

በዘርፉ የፖሊሲ ማሻያዎችን ጨምሮ በእውቀትና ክህሎት ላይ የተመሰረተ የሰራተኛ ቅጥር በማካሄድና የተለያዩ ማሻሻያዎችን በማድረግም ዘርፉን ለማሳደግና ለማዘመን ጥረት እንደሚደረግም ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በገንዘብ ተደልለውና በሙስና እና ብልሹ አሰራር ሳቢያ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት መሞከር እንደሌለባቸውም አንስተዋል።

ባለሃብቱም ተግቶ በመስራት፣ ግብርን በአግባቡ በወቅቱ በመክፈል እንዲሁም ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት እንቅስቃሴ ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቅሰው፥ መንግስትም ሃላፊነቱን በአግባቡ ይወጣል ብለዋል።

 


በዳዊት መስፍን