ኢትዮጵያና የተመድ የሠላም ማስከበር ጉዳዮች ተባብረው ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 8 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሠላም ማስከበር ጉዳዮች በዓለም አቀፍ የሠላም ማስከበር እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ተባብረው ለመስራት ተስማሙ።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ፥ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሠላም ማስከበር ጉዳዮች ምክትል ዋና ፀሀፊ ጃን ፒዬር ለክሮክስ ጋር ተወያይተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታዋ በዚህ ወቅት፥ የሠላም ማስከበር ዘመቻዎች ስኬት ተቋማትን የማጠናከር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያም የምትሳተፍባቸው የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች እንዲሳኩም አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።

የተመድ የሠላም ማስከበር ጉዳዮች ምክትል ዋና ፀሀፊ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ የሠላም አስፈፃሚዎች ተልዕኮ የማስፈፀም ብቃትና ቁርጠኝነትን አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት የምትሰጠውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል መጠየቃቸውንም ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።