የአፍሪካ የነፃ ንግድ ቀጠና ስምምነት ለኢትዮጵያ ምን ይፈይዳል?

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነትን መፈረሟ በቀጣይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ በኩል አወንታዊ ተፅእኖ እንደሚኖረው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ገለፁ።

የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለው የእርስ በእርስ የንግድ ግንኙነት 16 በመቶ ገደማ ነው።

ይሁን እንጂ ይህ አሃዝ የአውሮፓ ሀገራት የእርስ በእርስ የንግድ ግንኙነት ከደረሰበት 60 በመቶ ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው።

በመሆኑም የአፍሪካ ሀገራት ከስድስት ዓመት በፊት በአውሮፓውያኑ 2012 ጀምረው አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ለመፍጠር ሀሳብ አቅርበው ሲወያዩ ከርመዋል።

በዚህም በርዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደው አስችኳይ የመሪዎች ስብሰባ 44 ሀገራት ትናንት ይህን ስምምነት ፈርመዋል።

ኢትዮጵያም የዚህ ነፃ የንግድ ቀጠና አካል ለመሆን ስምምነቱን ፈርማለች።

ይህን ስምምነት ከፈረሙት ሀገራት ግማሽ እና ከዚያ በላይ ያህሉ የሀገራቸው ህግ አድርገው ካፀደቁት ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምር መረጃዎች ያመለክታሉ።

ስምምነቱ ሀገራት ከሌላ የአፍሪካ ሀገር በሚያስገቡት ሸቀጥ ላይ ከጣሉት ቀረጥ ውስጥ 90 በመቶን እንዲያነሱ ያስገድዳል።

ለመሆኑ ኢትዮጵያ ከዚህ ስምምነት ምን ትጠቀማለች? በእርግጥ ስምምነቱስ በፍጥነት ተግባራዊ የመሆን እድሉ ምን ያህል ነው የሚል? ጥያቄ ይነሳል።

በኢትዮጵያ ልማት ምርምር ተቋም የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር በሪሁ አሰፋ፥ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ለውጥ ለማድርግ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ተናግረው፥ አሁን የፈረመቸው ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት በቀጣይ ዓመታት ላነገበችው አላማ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልፀዋል።

ዶክተር በሪሁ ኢትዮጵያ ግዙፍ የገበያ ድርሻ የሚፈጥረውን ስምምነት መፈረሟ አሁን ላይ ያለውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው የሚመጡ አለም አቀፍ ኩባንያዎችን ፍላጎት የሚያሳድግ ነው ብለዋል።

ይህ ደግሞ የሀገሪቱን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት በቀጣይ አራትና አምስት ዓመታት ውስጥ የሚያሳድገው ነው ይላሉ።

ዋና መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የኢንቨስትመንት ኩባንያ ፌርፋክስ አፍሪካን ፈንድ ግሎባል ሊቀመንበር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በማምረቻው ዘርፍ ምቹ ሁኔታ ያላት መሆኑ ተወዳዳሪነቷን ከፍ እንደሚያደርገው ገልፀዋል።

በዚህም ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ፈጣን ጥቅም ላያመጣ ቢችልም በቀጣይ ዓመታት ግን ትልቅ ጥቅም ያመጣል ባይ ናቸው።

ለዚህም በግብርና ምርቶች ላይ እሴት ለመጨመር የሚደረገው እንቅስቃሴ ሲጠናከር ይህ ግዙፍ ገበያ ለሀገሪቱ አስትዋፅኦው ሰፊ ነው ብለዋል።

የምጣኔ ሀብት ምሁር ፕሮፌሰር ፍስሀፅዮን መንግስቱ ደግሞ፥ አፍሪካዊያን ወደ ነፃ የንግድ እንቅስቃሴው ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ሊያሟሉት የሚገባው የቤት ስራ አለ ይላሉ።

እርሳቸው “የሰዎች ነፃ ዝውውር ሳይኖር እንዴት ነፃ የንግድ እንቅስቃሴ በፍጥነት ገቢር ይሆናል?” የሚል ጥያቄ በማንሳት ይህንን መተግበር እንደ ቀዳሚ ሁኔታ ያስቀምጣሉ።

በአፍሪካ ህብረት ድረ ገፅ ላይ የሰፈረው መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ አሁናዊው የአፍሪካ እንቅስቃሴ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ነው።

አህጉሪቷ የተከፋፈለችባቸው ክፍለ አህጉራዊ ተቋማት አንድ የምጣኔ ሀብት ውህደት ለመፍጠር ራሳቸውን በመሰረተ ልማት እያስተሳሰሩ ነው።

ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጠና በራሱም በርካታ ሀገራት በመንገድ እና በቧቡር ትራንስፖርት እየተሳሰሩ ነው።

በአፍሪካም ባለፈው የመሪዎች ስብሰባ ወቅት የአፍሪካን የአየር ክልል ለአፍሪካዊያን አየር መንግዶች ነፃ እንዲሆን ተስማምቷል።

 

 

በስላባት ማናዬ