ከውጭ ምንዛሪ ተመን ማሻሻያ ጋር እኩል የዋጋ ማሻሻያ አለመደረጉ የግዥ ስርዓቱ ላይ እንቅፋት እየፈጠረ ነው

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 10 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ከውጭ ምንዛሪ ተመን ማሻሻያ ጋር እኩል የዋጋ ማሻሻያ ባለመደረጉ የግዥ ስርዓቱ ላይ እንቅፋት መፍጠሩን የመንግስት ግዥ እና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አስታወቀ።

የፌደራል ግዥ እና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ፥ ለሶስት አመት የሚቆይ የግዥ ማዕቀፍ ስምምነት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ መደረጉን ተናግረዋል።

ባለፉት አመታት አቅርቦቱ በተያዘለት ጊዜ እና ጥራት ሲቀርብ ቢቆይም፥ ካለፈው ጥቅምት ጀምሮ ግን አብዛኛዎቹ አቅራቢዎች በገቡት ውል መሰረት እያቀረቡ አለመሆኑንም ነው የሚናገሩት።

ለዚህ ደግሞ የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን በ15 በመቶ መዳከምን ተከትሎ ለአቅራቢዎች የዋጋ ማሻሻያ አለመደረጉ ዋና ምክንያት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የአገልግሎቱ ምክትል ኮሙዩኬሽን ሀላፊ አቶ አሰፋ ሰለሞን በበኩላቸው፥ የማዕቀፍ ስምምነቱ ለሶስት አመት የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

አገልግሎቱ የማዕቀፍ ግዥ ስምምነቱን ለ180 የፌደራል ተቋማትና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚያደርግ ሲሆን፥ በስምምነቱ መሰረትም በየአመቱ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ 300 አይነት ቁሳቁሶች ይቀርባሉ።

በዚህ ስምምነት እቃዎችን ለማቅረብ 49 ድርጅቶች ከአገልግሎቱ ጋር ውል ቢያስሩም አሁን ላይ በተለይም 10 የሚሆኑት አቅራቢዎች በውላቸው መሰረት እያቀረቡ አይደለም ነው የተባለው።

የማዕቀፍ ስምምነቱ በየሶስት ወሩ የዋጋ ማሻሻያ እንደሚደረግ በውሉ ላይ ተቀምጧል፤ በአንጻሩ የፌደራል የመንግስት ግዥ አፈጻጸም መመሪያ ደግሞ የዋጋ ማስተካከያው ጨረታው ሲከፈት በነበረው ወቅታዊ ዋጋ ላይ ተመርኩዞ ልዩነት መኖሩ ከማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ሲረጋገጥ ይደረጋል ይላል።

በዚህ ምከንያት ከ2008 ጀምሮ እነዚህ እቃዎች ላይ የዋጋ ማሻሻያ አልተደረገባቸዉውም፤ ለዚህ ደግሞ እቃዎቹ ከተገዙበት አንጻር አሁን ላይ ከ25 እስከ 30 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ልዩነት መታየቱ ምክንያት መሆኑን የህዝብ ግንኙነት ምክትል ሃላፊው ይናገራሉ።

የመንግስት ግዥ እና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ፥ ችግሩ በሁለት መንገድ የሚፈታ ነው ይላሉ።

በተደረገው የውጭ ምንዛሪ ተመን ማሻሻያ መጠን ለአቅራቢዎች የዋጋ ማስተካከያ በማድረግና፥ ይህ ካልተሳካ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አስቸኳይ የሆኑ ግዥዎችን በራሳቸው እንዲፈፅሙ ማድረግ የተያዘ አቅጣጫ እንደሆነም አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈ ግን አሁን ላይ ከግዥ ስርዓቱ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሰራ ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ።

አገልግሎቱ ከ2003 ዓ.ም ወዲህ ከ60 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የማዕቀፍ እና የተለያዩ ሀገራዊ እና ስተራቴጅካዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ቁሳቁሶች ግዥ ፈፅሟል።
ባሳለፍነዉ ግማሽ አመት ደግሞ ከ7 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ ግዥዎችን ለመፈፀም ስምምነቶችን አድርጓል።

 

 

 

በተመስገን እንዳለ